Search

"ኔሞ" የሽናሻ ብሔረሰብ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት

ሰዎች በሚያደርጓቸው ማኅበራዊ መስተጋብር ውስጥ በሚያጋጥም አለመግባባት ግጭት ሊከሰት ይችላል፡፡

እነዚህን ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትም በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከናወኑ ባሕላዊ የግጭት  አፈታት ሥርዓቶች አሉ፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኙ ሽናሻ ማህበረሰብ ዘንድ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ የተጣሉት ሰዎች ችግራቸውን የሚፈቱት "ኔሞ" በተሰኘው ሀገር በቀል ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ነው። 

ይህ የዳበረ የግጭት አፈታት ሥርዓት  “ኔሞ” ሽናሾች ግጭት ከመከሰቱ አስቀድመውም የሚከላከሉበት መሳሪያቸው መሆኑን የብሔረሰቡ ሽማግሌዎች ለኢቲቪ ገልጸዋል።

ነገር ግን ግጭት ከተከሰተ እና ጉዳት ከገጠመ ጉዳዩ በ "ኔሞ"  የባሕላዊ ግጭት አፈታት ሥርዓት የሚዳኝ እንደሚሆን ነው የተናገሩት። 

በዚህም ቤተሰብ ከቤተሰብ፣ ጎረቤት ከቤተሰብ፣ ጎረቤት ከማህበረሰብ ጋር ወይም ግለሰብ ከግለሰብ በሚጋጩበት ጊዜ የጎሳ እና የማህበረሰብ ሽማግሌዎች ተገኝተው ግጭቱ የተፈጠረበት ምክንያት ከሥር መሰረቱ ተብራርቶ ይቀርባል። 

ሽማግሌዎቹም ጉዳዩን ደረጃ በደረጃ ካዩ በኋላ፣ ጥፋት የተገኘበት አካል በሽማግሌዎቹ ፊት  እግር ላይ ወድቆ ይቅርታ እንዲጠይቅ ይደረግና ጥፋቱን አምኖ ካሳ እንዲከፍል ይደረጋል። 

በዚህ ባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት መሠረት በዳዩንም ተበዳዩንም የሚያሳምን ፍርድ በመስጠት ምንም አይነት ቁርሾ  እንዳይኖር በማድረግ የሚከናወን መሆኑ ይገለጻል።

የ"ኔሞ" ባሕላዊ የግጭት አፈታትሥርዓት  አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ቂም እና በቀልን ሳይወልዱ በፊት ቀድሞ እርቅ የሚከናወንበት በመሆኑ ለዘመናዊው የፍትሕ ሥርዓትም ትልቅ አስተዋፅኦ ያው እያበረከተ መሆኑ ይጠቀሳል። 

በሔለን ተስፋዬ