Search

ድርቅን በመቋቋም የምግብ ዋስትና እየሆነ ያለው እንሰት

እንሰት በሀገራችን በርካታ አካበቢዎች ከጥንት ጀምሮ ለምግብነት እየዋለ የሚገኘ ተክል ነው።  ተክሉ ከምግብነት ባለፈ ለመድኃኒትነት ተፈላጊ እንደሆነ ተጠቃሚዎቹ ያነሳሉ።

ታድያ የዚህ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ተክል ዝሪያ ላይ እያጋጠመ ያለውን በሽታ እና ሌሎች ችግሮች፤ በምርምር ለማሻሻል እየተሰራ ያለው ሥራ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ምርታማነቱ ላይ ትልቅ ትጽእኖ በማሳደር ላይ ይገኛል።

ለእንሰት የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆን፣ የበሽታ መስፋፋት፣ የችግኝ እጥረት፣ ለእንሰት ምርምር የሚሰጠው በጀት አነስተኛ መሆን፣በምርምር የተገኙ ውጤቶችን በኤክስቴሽን አስደግፎ ወደ አርሶ አደሩ የማድረስ ውስንነቶች ከብዙ በጥቂቱ የሚነሱ ችግሮች  ናቸው።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ደጋማ ወረዳዎች ከጥንት ጀምሮ ለምግብነት እየዋለ የሚገኘው እንሰት ዘሩን ለማቆየት አርሶ አደሩ ብዙ ጥንቃቄዎችን እያደረገ ይገኛል።

ጠባብ የመሬታ ይዞታ ባለባቸው የዞኑ አካባቢዎች አርሶ አደሩ የሕይወቱ መሰረት፣ የምግብ ዋስትናው ደጀን የሆነውን እንሰት ተንከባክቦ ለመያዝና ለመጠቀም ለዘመናት ያቆየውን የአያያዝ  መንገድ ዛሬም ይጠቀምበታል።

ፈተናዎቹ ብዙ ቢሆንም ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የእንሰት ዝሪያዎችን በማምረት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የስልጤ ዞን /አስተዳደርና ግብርና መምሪያ ኃላፊ ሙበራ ከማል ናቸው።

ኃላፊው በሽታን መቋቋም የሚችሉ እና የመድኃኒትነት ባህሪ ያላቸውን የእንሰት ዝሪያዎችን በማስፋት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የእንሰት ዝሪያዎችን በማምረት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግም፤ 1200 ሄክታር በላይ መሬት በየዓመቱ በአዲስ የእንሰት ተክል እንደሚሸፈንም ነው ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር በነበራቸው ቆይታ የገለጹት።

እስካሁን በዞኑ 16 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በእንሰት ተክል መሸፈኑንም አንስተው፤ 1.7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት በየዓመቱ በአማካይ እየተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለአብነትም በዞኑ የአሊቾ ውሪሮ ወረዳ 6ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ የእንሰት አይነቶች መሸፈኑን የገለጹት ኃላፊው፥ በሄክታር እስከ 440 ኩንታል ምርትም እየተሰበሰበ ይገኛልም ብለዋል።

በስልጤ ዞን አልቾ ውሪሮ ወረዳ በሁሉም ቀበሌዎች የእንሰት ምርትን ለማስፋት፤ የእንሰት ዝርያን በመለየት በዘጠኝ ቀበሌዎች እንዲሁም በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ጣቢያዎች የማባዛት ሥራ እየተከወነ መሆኑንም ነው ያነሱት።

አርሶ አደሩ ከራሱ ፍጆታ ባለፈ የእንሰት ምርቶችን ለማዕከላዊ ገበያ እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን፤ እንሰትን ከደጋማ ወረዳዎች ባለፈ በቆላማ ወረዳዎች የዛፍ ተክሎች በነበሩበት አካባቢ እንሰት የማስፋፋት ሥራም እየተሰራ ይገኛል ተብሏል።

በስልጤ ዞን  በደጋማ ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ዘላቂ ኢኮኖሚን እውን ለማድረግ በጓሯቸው የእንሰት ችግኝን በብዛት እና በጥራት በማፍላት ለገበያ እያቀረቡ እንደሆነም ተገልጿል።

በአልቾ ውሪሮ ወረዳ ከሚገኙ እና ለምግብነት እንዲሁም ለመድሀኒትነት ከሚውሉ የእንሰት ዝርያዎች ውስጥ ቤንዤ ፣ከምባታ፣ ቅምናር፣ አጋዴ እና አስታራ ተጠቃሾች ናቸው።

የእንሰት ተክል በከፍተኛ ሁኔታ እሴት ተጨምሮበት ለምግብነት ከሚውሉ ከቆጮ፣ከቡላ፣ከአተካኖ እና ከአሚቾ  ባሻገር፤ ተረፈ ምርቱ የቤት ቁሳቁሶችን  ለማዘጋጀትና ለዘርፈ ብዙ አገልግሎት ይውላል።

በመሀመድ ፊጣሞ