Search

መጋቢት፤ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትንሣኤ ምዕራፍ

እሑድ መጋቢት 20, 2018 198

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጋቢት 24 ቀን 2003 . የመሠረት ድንጋዩ ሲቀመጥ፣ ለኢትዮጵያውያን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ተስፋን ያበሰረ ብሔራዊ ኩራት ሆኖ ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ታላቅ ተስፋ እስከ መጋቢት 2010 . ድረስ በነበሩት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ የአስተዳደር ብልሽት፣ በሙስና እና በውጭ ዲፕሎማሲያዊ ሤራዎች ተተብትቦ ለከፍተኛ ውድቀት ተጋልጦ ቆይቷል።

60 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማያገኝበት እና መቶ በመቶ የሚሆነው የግብፅ ሕዝብ የኃይል ተጠቃሚ በሆነበት ተጨባጭ ሁኔታ፣ ይህን -ፍትሐዊነት ለመቀልበስ የተጀመረው ፕሮጀክት በገጠሙት ውስጣዊ እና ውጫዊ ጫናዎች ምክንያት ለዓመታት ተገትሮ ለመቆየት ተገድዶ ነበር።

በወቅቱ የግድቡ ግንባታ በቴክኒክ እና በፋይናንስ ረገድ እጅግ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱም በውድቀት አፋፍ ላይ ይገኝ ነበር።

የሲቪል ግንባታ ሥራውን የያዘው ሳሊኒ የግንባታውን ሂደት 80 በመቶ በላይ አድርሶታል። ወሳኝ የሆነውን የኤሌክትሮሜካኒካል ሥራ የተረከበው ሜቴክ ግን ሥራውን 25 በመቶ ማጠናቀቁን ሪፖርት ቢያደርግም እውነታው ግን ሌላ ነበር። 

ሜቴክ ከሠራው ሥራ ውስጥ በመሬት ላይ ያለው ክንውን 2 በመቶ የማይበልጥ እንደነበር ተረጋግጧል። ይህ ክፍተት በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥን የፈጠረ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በሙስና መተብተቡ የሕዝቡን የሥነ-ልቦና አንድነት ክፉኛ ፈትኖታል።

የግንባታው ስድስተኛ ዓመት በሆነው በመጋቢት 2010 . በሀገራችን የመጣው የፖለቲካ ለውጥ፣ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዳግም ሕይወት የዘራ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ሆነ።

የለውጡ መሪዎች ለፕሮጀክቱ በሰጡት ቀዳሚ ትኩረት መሠረት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ግንባታውን በአካል በቦታው ተገኝተው በመገምገም መሠረታዊ ችግሮቹን ለይተዋል። ቀጥሎም ግድቡ ላይ ሕይወት የሚዘሩ ውሳኔዎችን በቁርጠኝነት ወስነዋል።

ሜቴክን ከግንባታው ሂደት በማሰናበት ፕሮጀክቱን ወደ ሙያዊ መስመር እንዲመለስ የተላለፈው ውሳኔ፣ ቴክኒካዊ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያንን የሥነ-ልቦና ትንሣኤ ያበሰረ እርምጃም ነበር።

መንግሥት ፕሮጀክቱን ወደ ትክክለኛው መስመር ሲመልስ "ግድቡ ተሽጧል" የሚል የሐሰት ወሬ በመንዛት ሀገራችንን ለማናጋት የሞከሩ ውስጣዊ ተላላኪዎች ቢኖሩም፣ የሥራው ውጤት ግን የሕዝቡን ተስፋ ዳግም እንዲያንሰራራ አድርጓል።

ከዚህም ባለፈ ግብፅ ጉዳዩን የዓለም አቀፍ የፀጥታ ሥጋት አስመስላ ወደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እና ወደ አሜሪካ በመውሰድ ከፍተኛ ጫና አሳድራለች።

የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ "ግብፅ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች" የሚል የማስፈራሪያ ንግግር ቢያደርጉም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ ላይ እንደማትደራደር በመግለጽ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲመለስ አድርገዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በተካሄዱት ታሪካዊ መድረኮች፣ ኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድልን አስመዝግባለች። የወቅቱ በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ አምባሳደር ታየ አጽቀሥላሴ (የአሁኑ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት) የጸጥታው ምክር ቤት የውኃ ጉዳይን የማየት ሥልጣን እንደሌለው በመግለጽ የግብፅን ሤራ አክሽፈዋል።

በተመሳሳይ የወቅቱ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር / ኢንጂነር ስለሺ በቀለ "ኢትዮጵያውያን ከዓባይ የመጠጣት መብት የላቸውምን?" የሚል ዓለምን ያስደመመ ጥያቄ በመሰንዘር የግድቡን ፍትሐዊነት በቴክኒካዊ እና በሞራል ማስረጃዎች ለዓለም ማኅበረሰብ አስረድተዋል።

ተስፋቸው የለመለመው በውጭ እና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም "ግድቡ የኔ ነው!" በሚል ብሔራዊ ንቅናቄ የገንዘብ እና የሞራል ድጋፍ በማድረግ፣ እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎች በግንባታው አካባቢ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ፕሮጀክቱን በጽናት ጠብቀውታል። ይህ የተቀናጀ የፖለቲካ አመራር፣ የዲፕሎማሲ ጥንካሬ እና የሕዝብ ተሳትፎ ታላቁን ግድብ ለዛሬው የስኬት ምዕራፍ አብቅቶታል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቆራጥ አመራር እና በባለሙያዎች ብቃት ግድቡ አሁን ላይ የደረሰበት ደረጃ፣ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎች በአሸናፊነት መወጣት እንደምትችል ማሳያ ሆኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የግድቡን መጠናቀቅ ይፋ ባደረጉበት ወቅት፣ ከግድቡ በፊት እና በኋላ ያለችው ኢትዮጵያ አንድ እንዳልሆኑ መግለጻቸው ፕሮጀክቱ የሀገራችንን የሥነ-ልቦና እና የልማት አቅጣጫ የቀየረ መሆኑን ያረጋግጣል።

በመሆኑም መጋቢት ወር የግድቡ ውልደት ብቻ ሳይሆን፣ ፕሮጀክቱ ከውድቀት አፋፍ ተመልሶ ለድል የበቃበት እና የሕዝቡ ተስፋ የታደሰበት የትንሣኤ ወር ሆኖ በኢትዮጵያ ታሪክ ይዘከራል።

በለሚ ታደሰ