በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የኮሪደር ልማቶች፣ የወንዝ ዳርቻዎችና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ለሰርከስና ለኪነ-ጥበብ ዘርፉ መጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
በአዲስ አበባ ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የሰርከስ ፌስቲቫልና ውድድር በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀምሯል።
“የሰርከስ ጥበብ ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው የሰርከስ ፌስቲቫልና ውድድር ከመጋቢት 21 እስከ 24 ቀን ድረስ ለተከታታይ አራት ቀናት ይቆያል።
ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር ዓባይ በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በከተማዋ የተገነቡ የመሠረተ ልማት አውታሮች ለዘርፉ ዕድገት ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን ገልጸው፣ ዘርፉን ከገጽታ ግንባታ ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ ፋይዳም በሰፊው እየተጠቀምንበት እንገኛለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሰርከስ ጥበብ ከፍተኛ ዕድገት እያሳየ መሆኑን የገለጹት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባየ በበኩላቸው፤ ዘርፉ የሀገርን ገጽታ ለዓለም በማስተዋወቅና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሰርከስ የመጪው ዘመን የኢትዮጵያ መገለጫ የጥበብ መስክ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ጥበቡ የወል እውነትንና ህብረ-ብሔራዊነትን በማንፀባረቅ ረገድ ትልቅ የሀገር ገጽታ መገንቢያ ሆኖ እያገለገለ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል።