Search

የኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ የለውጥ ሞተር፡ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና

እሑድ ግንቦት 09, 2018 176

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢንዱስትሪ መሥራች እና ዋነኛ ማዕከል ለማድረግ መንግሥት በነደፈው አርቆ አሳቢ ስትራቴጂ ውስጥ  የኢንዱስትሪ ፓርኮች የልማቱ የጀርባ አጥንትና የለውጥ ዋና ሞተር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

ፓርኮቹ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ውስጥ ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ማኑፋክቸሪንግ የሚደረገውን ታሪካዊ መዋቅራዊ ሽግግር በማፋጠን ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው ሚና እያበረከቱ ሲሆን፣ ለግሉ ዘርፍ መነቃቃትም አዲስ የብርሃን በር ከፍተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እነዚህን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናነት (SEZs) በማሳደግ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ይበልጥ ለማጎልበት እና ግዙፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ስኬታማና ተስፋ ሰጪ ሥራዎች በከፍተኛ ስሜት እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች፡ ከቀረጥ ነፃ ዕድል ወደ አፈጻጸም ተኮር ድጋፍ

በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለሚሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች የሚደረገው ድጋፍ እና የማበረታቻ ሥርዓት በቅርቡ ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መዋቅራዊ ለውጥ መሻሻሉ ትልቅ አቅም ሆኗል፡፡

የቀድሞው አሠራር በዘርፍ እና በቦታ ላይ ብቻ የተገደበ ሰፊ የግብር ነፃ ዕድል ይሰጥ የነበረ ሲሆን፣ አዲሱ የፖሊሲ አቅጣጫ ግን ይህንን አሠራር በውጤት እና በአፈጻጸም ላይ ወደተመረኮዘ ዘላቂ ድጋፍ አሳድጎታል፡፡

በዚህም መሠረት ባለሀብቶች በሚያሳዩት የላቀ አፈጻጸም ልክ እስከ 15 በመቶ የሚደርስ ዝቅተኛ የድርጅት ገቢ ግብር ለረጅም ጊዜ እንዲከፍሉ የሚደረግ ሲሆን፣ በተለይም በልዩ የኢኮኖሚ ቀጣናዎች ውስጥ ለሚሰማሩ አልሚዎች 10 ዓመታት የሚቆይ 5 በመቶ የገቢ ግብር ማበረታቻ ተመቻችቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የማምረቻ መሣሪያዎችን እና የፋብሪካ ግንባታ ቁሳቁሶችን ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ የማስገባት መብት አሁንም በሥራ ላይ መሆኑ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን በከፍተኛ ደረጃ እያገዘው ይገኛል፡፡

 "ኢትዮጵያ ታምርት" እና የገቢ ምርት ተኪነት ስኬቶች

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ግንባር ቀደም መሪነት እየተመራ ያለው እና ሀገራዊ ኩራትን የሰነቀው "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄም፣ የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካትን ታላቅ ዓላማ በተጨባጭ ድሎች እያስገኘ ይገኛል፡፡

 2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ 4 ነጥብ 85 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት የገቢ ምርትን ጥራት ባላቸው የሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት መቻሉ የዚህ ማሳያ ነው፡፡

 ለዚህ ታላቅ ሀገራዊ ድል መመዝገብ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በስፋት እና በጥራት ወደ ማምረት የገቡ አዳዲስ ፋብሪካዎች ሚና እጅግ የጎላ ነው፡፡

በተለይም በፓርኮች ውስጥ በገቢ ምርት ተኪነት ረገድ የታቀደው 46ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም አፈጻጸሙ ግን 70 ሚሊዮን ዶላር በመሆን ዕቅዱን በከፍተኛ ደረጃ አብልጦ አከናውኗል፡፡

 ይህ አስደናቂ ስኬት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ 10.1 በመቶ ዕድገት እንዲያስመዘግብ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፡፡ ቀደም ሲል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጥቶባቸው ከውጭ ሀገር ይገቡ የነበሩ እንደ መከላከያ እና ፖሊስ አልባሳት፣ ዘመናዊ የውኃ ቆጣሪዎች፣ እንዲሁም የተለያዩ የምግብ እና መጠጥ ውጤቶች አሁን ሙሉ በሙሉ በሀገራችን የፋብሪካ ውጤቶች እየተመረቱ ይገኛሉ፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የኤክስፖርት አፈጻጸም

የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ለሀገራችን ወጣቶች፣ በተለይም ለሴቶች እህቶቻችን ሰፊና ዘላቂ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴትነቱን በተግባር አስመስክሯል፡፡

 በሦስተኛው 100 ቀን የሥራ አፈጻጸም ዑደት ውስጥ ብቻ በፓርኮች ውስጥ 10 ሺህ 757 ዜጎች አዲስ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡

ከዚህ ውስጥ አብዛኛው የሥራ ዕድል ለወጣት ሴቶች የተመቻቸ በመሆኑ ማኅበረሰብን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በግልጽ አረጋግጧል፡፡

በኤክስፖርት ዘርፍም ቢሆን በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያለውን ተለዋዋጭና ተፈታታኝ ሁኔታ በጥራት በመቋቋም፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች 7.7 ሚሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ገቢ መገኘቱ የምርት ጥራታችን ዓለም አቀፍ ደረጃን እያሟላ መምጣቱን ያበስራል፡፡

ለዘላቂ ኢኮኖሚ የተነደፉ የኢኮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች እና የዲጂታል ሽግግር

የኢንዱስትሪ ልማታችን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሻገር ዘላቂ መሠረት እንዲኖረው፣ መንግሥት የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ የሚጠቀሙ፣ ብክለትን የሚቀንሱ እና የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓታቸው ዘመናዊና ስነ-ምህዳራዊ የሆነ "የኢኮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮችን" የመገንባት ታላቅ ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን (IPDC) በፓርኮች ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን (EV) ለትራንስፖርት አገልግሎት በስፋት በማሰማራት፣ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ በተግባር ለዓለም እያሳየ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከቀላል የጨርቃጨርቅ ምርቶች ባለፈ እንደ ፋርማሲዩቲካል፣ ኬሚካል እና ብረታ ብረት ያሉ ከፍተኛ ቴክኖሎጂ እና ዕውቀት የሚጠይቁ ምርቶችን ወደማምረት በልበ ሙሉነት እየተሸጋገሩ ነው፡፡

ምንም እንኳን የዓለም አቀፍ ሎጂስቲክስ እና የውጭ ምንዛሬ ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች ቢኖሩም፣ "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ ያስመዘገበው ድል እና አዲሱ የልዩ የኢኮኖሚ ቀጣና ማዕቀፍ፣ ሀገራችን የጀመረችው የኢንዱስትሪ ብልጽግና ጉዞ ብሩህ፣ ስኬታማና ተስፋ ሰጪ መሆኑን በፅኑ ያረጋግጣሉ፡፡

በለሚ ታደሰ