የሐረርጌ ሕዝብ በመደመር የልማት እሳቤ እየተመራ በአዲስ የለውጥ ጎዳና ግስጋሴ ላይ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ። ሕዝቡ ልማት እና የአካባቢ ጥበቃን በንቃት ከመተግበር ባሻገር፤ ከሰላም እና ከለውጥ ጋር ለመተባበር ልቡ የቀና መሆኑንም አብራርተዋል። አካባቢው ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የዕርዳታ ጠባቂ የነበሩበት ቢሆንም፤ አሁን ላይ መንግሥት ለግብርና በሰጠው ልዩ ትኩረት በስንዴ፣ በቆሎ እና በተለያዩ ፍራፍሬዎች የልማት ሥራዎች ተጠናክረው በመሠራታቸው የተረጂዎችን ቁጥር ወደ መቶ ሺሕ ዝቅ ማድረግ መቻሉን አድንቀዋል።
የሐረርጌ አርሶ አደሮች በላባቸው ሀገርን በመቀየር እና ራስን በመቻል ለሌሎች አርአያ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በሐረርጌ የተሠሩ የልማት ሥራዎች ከሐረርጌ አልፈው፣ የውኃ አቅርቦት ድጋፍ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ዘልቆ በመግባት የሐረርጌ አባቶች እና ወጣቶች አሻራ በመላው ኢትዮጵያ ማስተጋባቱን ጠቅሰዋል።
ሕዝቡ የጀመረውን የልማት ጉዞ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና የተተከሉትን ችግኞች እንዲንከባከብ ያሳሰቡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫም ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በመሳተፍ ለሥራ እና ለልማት የሚያነሣሣውን እና ‘ሁሌ እንሥራ’ የሚለውን ብልጽግና ፓርቲ እንዲመርጥ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በድህነት፣ በግጭት እና በኋላቀርነት የምትታወቅበትን የታሪክ ምዕራፍ ዘግታ፣ አሁን በሥራ እና በለውጧ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን እያገኘች መምጣቷንም አስገንዝበዋል።
በቢታንያ ሲሳይ