Search

ከባህላዊ "ሼድ" ወደ ዘመናዊ ሕንጻ፡ የገላን ጉራ ልዩነት

ቅዳሜ ግንቦት 08, 2018 245

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ታሪክ ውስጥ ለረጅም ዓመታት የተለመደው አሠራር ሰፋፊ መሬቶችን አጥሮ፣ መሬት ላይ የተንጣለሉ ባለ አንድ ፎቅ "ሼዶችን" (Sheds) መገንባት ነበር። 
እነዚህ ባህላዊ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መነቃቃት የራሳቸውን አስተዋፅኦ ቢያደርጉም፣ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባሉ የመሬት እጥረት ባለባቸው ፈጣን አዳጊ ከተሞች ውስጥ ዘላቂነት ያለው ሞዴል አልነበሩም።

ዛሬ ግን ይህን አሮጌ አሠራር የሚሰብር፣ የመሬት አጠቃቀምንና የኢንዱስትሪ ልማትን በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ግዙፍ ማዕከል ዕውን ሆኗል። ይኸውም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የገላን ጉራ ኢንደስትሪያል ፓርክ ነው። 

ይህ ማዕከል ከሌሎች የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች በምን ይለያል? ከዓለም አቀፍ ተሞክሮስ አንጻር ምን ልዩ ገጽታ አለው? ለሀገርስ የሚሰጠው ፋይዳ ምንድን ነው? 

1. በሕንጻ ደረጃ የተገነባ የመጀመሪያው ፓርክ (Vertical Industrial Park)፦ በኢትዮጵያ ከተለመዱት አግድም የተንጣለሉ (Horizontal) ፓርኮች በተለየ፣ ገላን ጉራ በሕንጻ ደረጃ የተሠራ የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው። ይህ አሠራር የመሬት እጥረትን ከመፍታቱም በላይ፣ በአንድ ቦታ ላይ 442 የማምረቻ ቦታዎችን አቅፎ ይዟል። በመሬት ቆጣቢነቱና በቅልጥፍናው፣ ሲንጋፖር ከትንሽ ወደብ ከተማነት ወደ ዓለም የንግድና የቴክኖሎጂ ማዕከልነት ስትለወጥ የተጠቀመችበትን የ"Vertical Industrialization" ወይም የሕንጻ ላይ ኢንዱስትሪ ሥልት በሀገራችን ምድር በተግባር ያረጋገጠ ልዩ ሞዴል ነው።

2. ሁለንተናዊ ሥነ-ምህዳር (A Complete Ecosystem)፦ አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚያተኩሩት በማምረቻ ቦታ (ሼድ) አቅርቦት ላይ ብቻ ነው። ገላን ጉራ ግን ፋብሪካን ብቻ ሳይሆን ሰውንም ማዕከል ያደረገ "ሁለንተናዊ ሥነ-ምህዳር" የፈጠረ ነው። እናቶች በሥራቸው ላይ ሙሉ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያስችል የህጻናት ማቆያ (Daycare)፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን የሚያፋጥኑ የምርምርና ጥናት ማዕከላት (R&D)፣ እንዲሁም አምራቾች ምርቶቻቸውን ለሸማቾችና ለውጭ ገዥዎች በቀጥታ የሚያስተዋውቁበት ሰፊ የኤግዚቢሽንና የገበያ ማሳያ ቦታዎች በአንድ ጣሪያ ስር ተካተዋል። ይህ ከደቡብ ኮሪያ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክሶች ጋር የሚመሳሰልና ለኢትዮጵያ አዲስ የሆነ አሰራር ነው።

3. መሠረተ ልማት እና የኃይል ሉዓላዊነት፦ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ትልቁ ራስ ምታት የኃይል መቆራረጥ እና የውኃ እጥረት ነው። ገላን ጉራ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ሙሉ በሙሉ ራሱን የቻለ ሥርዓት ገንብቷል። የውኃ አቅርቦቱ ከውጭው መሥመር የሚጠበቅ ሳይሆን ራሱን የቻለ የከርሰ ምድር ውኃ ምንጭ አለው። የኃይል መቋረጥ እንዳይኖር 1250KVA ኃይል ማመንጨት የሚችሉ ግዙፍ ትራንስፎርመሮች፣ የነዳጅ ታንከሮች፣ እንዲሁም ዘመናዊ የመብራትና የኢንተርኔት መስመሮች ተሟልተውለታል። ይህ አስተማማኝነት አምራቾች ያለ አንዳች መቆራረጥ 24 ሰዓት እንዲያመርቱና የምርት ወጪያቸውን በእጅጉ እንዲቀንሱ ያደርጋል።

4. የከተማ ኢንዱስትሪያላይዜሽን እና አረንጓዴ ልማት፦ ብዙውን ጊዜ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲታሰቡ የጭስ፣ የቆሻሻ እና የብክለት ምስል ወደ አእምሯችን ይመጣል። በመሆኑም ከከተማ ራቅ ብለው እንዲገነቡ ይደረጋል። የገላን ጉራ ፓርክ ግን የአዲስ አበባን የከተማ ገጽታ በሚያሳምር መልኩ በዘመናዊ የሕንፃ ዲዛይን የተዋበ ነው። ማዕከሉ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ፣ የድሬኔጅ ሥርዓት፣ ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ እና ሰፊ የአረንጓዴ ቦታዎችን አሟልቷል። ይህ የኢኮኖሚ ልማትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ያጣመረው አካሄድ፣ ዘመናዊ ከተሞች (እንደ ቻይናዋ ሼንዘን) የሚከተሉትን የ"Eco-Industrial Park" መርህ የተከተለ ነው።

ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች፦ የቁጭት ማብቂያ፣ የተስፋ መጀመሪያ የገላን ጉራ ኢንደስትሪያል ፓርክ የሀገራችንን የማምረት አቅም በማሳደግ ቁልፍ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ያመጣል።

የመጀመሪያው ፋይዳው የክላስተር (Cluster) ልማት ነው። 48 ደረጃቸውን የጠበቁ የብረታ ብረት፣ የእንጨት ውጤቶች እና የኬሚካል ፋብሪካዎች፤ እንዲሁም 68 ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የቆዳ፣ የጨርቃ ጨርቅ እና የፕላስቲክ ኢንዱስትሪዎች በአንድ ቦታ መሰባሰባቸው፣ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾች ከትላልቆቹ ጋር የግብዓትና የምርት ትስስር (Value Chain) እንዲፈጥሩ ያግዛቸዋል። አንዱ የሚያመርተው ለሌላው ግብዓት እየሆነ፣ የሎጂስቲክስ ወጪን አሳንሶ የጋራ ዕድገትን ያመጣል። በ2022 (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር) ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተነደፈውን የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ለማሳካት፣ ይህ ማዕከል ትልቅ ሞተር ነው።

ለዘመናት የውጭ ምርቶች ማራገፊያ፣ የስራ አጥነት ሰለባ እና "አስመጪ" በሚል አሳዛኝ ስም ስንጠራ የኖርንበትን የታሪክ ስብራት ጠግኖ፤ ዜጎችን ወደ ላቦራቶሪና ፋብሪካ በማስገባት በራሳችን ዐቅም እንድናመርትና ወደ ውጭ እንድንልክ መንገድ ይከፍታል።

በማጠቃለያው፣ ገላን ጉራ ኢንደስትሪያል ፓርክ ከብረትና ከሲሚንቶ የተገነባ ተራ ሕንጻ አይደለም። ይህ ማዕከል የኢትዮጵያ አዲስ የማሰብ አድማስ መገለጫ ነው። የመሬት አጠቃቀማችንን፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን እና የሥራ ባህላችንን ወደ ላቀ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሸጋገረ የዕድገት ዝላይ ነው። ዛሬ ይህ በቢሊዮኖች የተገነባ ማዕከል በራፉን ሲከፍት፣ አብሮ የሚከፈተው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት እና የብልጽግና በር ነው። የገላን ጉራ ሞዴል የፈነጠቀው ብርሃን መላ ሀገሪቱን አዳርሶ፣ ኢትዮጵያን  ከጥገኝነት አረንቋ ሙሉ በሙሉ እስክናወጣት ድረስ ዐቢይ የለውጥ ጉዟችን በጽናት ይቀጥላል።

 

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ