ኢትዮጵያ - የጥቁር ሕዝቦች ኩራት፣ የሥልጣኔ መነሻና የነፃነት ተምሳሌት ናት። ይህች ጥንታዊት ሀገር በታሪክ ማኅደር ውስጥ የነበራትን ገናናነት ዳግም ለማግኘት በምታደርገው ጉዞ፣ ከፊቷ የተጋረጡት ፈተናዎች ቀላል አይደሉም።
በተለይም የሀገራችን የሕልውና መሠረት ከሆኑት "ሁለቱ ውኃዎች" ማለትም ከታላቁ ዓባይ ወንዝ እና ከቀይ ባሕር ጋር ያላትን ተፈጥሯዊ ትሥሥር ለመበጠስ ለዘመናት የተጎነጎኑ ሴራዎች ዛሬም እንደ አዲስ አቆጥቁጠው ይታያሉ።
ኢትዮጵያ በዘመኗ የቀይ ባሕርን የንግድ መስመር የምትቆጣጠር ታላቅ የባሕር ኃያል ነበረች። ይሁን እንጂ ሀገራችንን ከባሕር ለማራቅ እና "የየብስ እስረኛ" ለማድረግ የተሠሩት ሥራዎች ጥንታዊ እና መሪር ናቸው።
ገና በ1550 ዓ.ም የኦቶማን ቱርኮች ምጽዋን በመያዝ ኢትዮጵያ ከቀጥተኛ የባሕር መስመር እንድትገለል በማድረግ የመጀመሪያውን የከበባ ሴራ ፈጽመዋል። ይህ ሴራ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በ1882 ዓ.ም የኢጣሊያ ቅኝ ገዥዎች በብሪታንያ ድጋፍ እና እውቅና ምጽዋን እና አሰብን በመያዝ የኢትዮጵያን የባሕር በር በይፋ የነጠቁበት ጥቁር የታሪክ ወቅት ተመዘገበ። ይህም ኢትዮጵያ ለዘመናት ለገነባችው የባሕር ኃይልና የውጭ ንግድ ትልቅ ፈተና አመጣ።
ፋሽስት ኢጣሊያ ሀገራችንን በወረረችበት በ1928 ዓ.ም ደግሞ፣ ወደብ አልባ መሆን ለሀገር ደህንነት ምን ያህል ስጋት እንደሆነ የታየበት ሌላው ክስተት ተፈጠረ። በወቅቱ በጅቡቲ በኩል ይመጡ የነበሩ የኢትዮጵያ የጦር መሣሪያዎች በፈረንሳይ ባለሥልጣናት ታገዱ፤ ይህም ሀገርን የመከላከል አቅማችንን ሽባ ለማድረግ ታስቦ የተሰራ ሴራ ነበር።
የዚህ የታሪክ ሰንሰለት እጅግ መሪር ውሳኔ የተላለፈው በ1983 ዓ.ም ነው። የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ በለንደን መግለጫ አማካኝነት ኢትዮጵያ ያለ ምንም የባሕር ኮሪደር ወይም የጣምራ ሉዓላዊነት ስምምነት ወደብ አልባ እንድትሆን ተደረገ። ይህ ውሳኔ የሀገራችንን የባሕር ኃይል ታሪክ በአንድ ጀንበር ያፈረሰ እና ኢትዮጵያን ለከፍተኛ የወደብ ኪራይና ለስትራቴጂያዊ ጥገኝነት የዳረገ "የጂኦግራፊያዊ እስር ቤት" ውሳኔ ተደርጎ ይወሰዳል።
የኢትዮጵያ ሁለተኛው የህልውና ደም-ስር ዓባይ ነው። ግብፅ የዓባይን ውኃ እንደ ግል ሀብቷ በመቁጠር "የሃይድሮ-ሄጂሞኒ" (Hydro-hegemony) ፖሊሲን ለብዙ ዓመታት ስትተገብር ቆይታለች። በ1921 እና በ1951 ዓ.ም በተፈረሙት የቅኝ ግዛት ውሎች ብሪታንያን፣ ግብፅንና ሱዳንን ብቻ ተጠቃሚ ለማድረግና ኢትዮጵያን ለማግለል የተሠራው ሥራ ሀገራችን በገዛ ውኃዋ ላይ ያላትን መብት ለማሳጣት የተዘረጋ ወጥመድ ነበር።
ከውል ማሰር ባለፈ፣ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የልማት ፕሮጀክቶችን እንዳታከናውን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ብድር እንዳይሰጡ ግብፅ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ስታደርግ ኖራለች። ይህ ሁሉ የሚያሳየው ኢትዮጵያ በውኃዎቿ ላይ ያላትን መብት እንዳታስከብር የተዘረጋውን ስልታዊ ከበባና ግልጽ ግፍ ነው።
ሰንሰለቱ ሲበጠስ
ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕርና ከዓባይ ለመነጠል የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ግባቸው አንድ ነው፤ እርሱም ሀገራችን ያላትን የተፈጥሮ ጸጋ ተጠቅማ የቀጣናው ልዕለ-ኃያል እንዳትሆን ማሰናከል! ይሁን እንጂ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ፣ የባሕር ኃይሉ ዳግም መደራጀት እና ወደ ቀይ ባህር ባለቤትነታችን ለመመለስ እያደረግናቸው ያሉ አስደናቂ የዲፕሎማሲ ጥረቶች ኢትዮጵያ ይህን የዘመናት የከበባ ሰንሰለት ሰብራ ለመውጣት ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ድሎች ናቸው።
ኢትዮጵያን ከእነዚህ ሁለት ውኃዎች ነጥሎ ማቆየት ለቀጣናው ሰላም የማይበጅና በታሪክም ሊቀጥል የማይችል መሆኑን የሀገራችን ወቅታዊ ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎች በተግባር እያረጋገጡ ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በሯን አስከብራ፣ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን መብት አረጋግጣ፣ ለምሥራቅ አፍሪካ ብልጽግና ዋስትና የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።