ዓለም በእንፋሎት ኃይል፣ በኤሌክትሪክ እና በኮምፒውተር አውቶሜሽን ሦስት ግዙፍ የኢንዱስትሪ አብዮቶችን ስታስተናግድ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በውስጥ ሽኩቻ፣ በተዘበራረቁ ፖሊሲዎችና በድህነት አረንቋ ውስጥ ታጥረን የሥልጣኔውን ባቡር በሩቁ ስንሸኝ ኖረናል።
የዓለም ሀገራት በፋብሪካ ጭስ እና በቴክኖሎጂ ግኝት ሰማይ ሲቧጥጡ፣ እኛ ያለንን የተፈጥሮ ጸጋ በባዕዳን እጅ እያስበላን፣ ላባችንን ገብረን ያመረትንበትን ጥሬ ዕቃ በሳንቲም እየሸጥን መልሰን በውድ ዋጋ ስንገዛ የኖርንባት የታሪክ ስብራታችን መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም።
ይህ የዘመናት የታሪክ እንቅልፍ፣ ዛሬ ላለነው ኢትዮጵያውያን ጥልቅ ቁጭትና አንገብጋቢ የለውጥ ጥማት የፈጠረ መሪር እውነት ነው።
ወደ ኋላ መለስ ብለን የኢንዱስትሪ ታሪካችንን ስንፈትሽ የባከኑ ዕድሎችን እናያለን። በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በውጭ ባለሀብቶች የተጠነሰሰው የኢንዱስትሪ ጅምር፣ እርሾ ሆኖ ዛሬ ላይ ከፍተኛ ደረጃ የሚያደርሰን የነበረ ቢሆንም በሥርዓቱ ባህርያዊ ችግር ምክንያት ከጅምር ማሳያዎች ያልዘለለ ዕድገት ሳያሳይ ቀርቷል።
በደርግ ሥርዓት "ካፒታል ከ500 ሺህ ብር ማለፍ የለበትም" በሚል አፋኝ ፖሊሲ የነበረችዋም ጅምር የግል ዘርፍ የሞት ጽዋ እንዲጠጣ ተደረገ።
በኢሕአዴግ ዘመን ደግሞ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው የነበረ ቢሆንም ዘርፉ ግልጽ የፖሊሲ አቅጣጫ ያልነበረው እና በስትራቴጂ ባለመመራቱ ዘርፉ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሲታነቅ እና በውጪ አቅራቢዎች እና ገበያ ጥገኝነት ሥር ሲማቅቅ ቆይቷል። ይህ የተቆራረጠ ጉዞ የኢንዱስትሪ ባለቤት ሳይሆን የባዕዳን ሸማች አድርጎን ኖሯል።
ዛሬ ግን ያ የቁጭት ዘመን እያበቃ ይገኛል። የዕድገቱን ባቡር ደረጃ በደረጃ ለመከተል ጊዜ የለንም። የአሁኑ ትውልድ እና አመራር ካለፈው የታሪክ ስብራት በመውጣት "የዝላይ ስልትን" በመከተል ዕጣ ፈንታውን በእጁ ቀርጿል። እኛ ያመለጡንን የድሮ አብዮቶች ለመድገም አንዳክርም፤ ይልቁንም በቀጥታ ወደ አራተኛው (ኢንዱስትሪ 4.0) እና አምስተኛው (ኢንዱስትሪ 5.0) የኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ተወንጭፈናል። ይህ "የቀድሞ መድረስ ሽልማትን" ያነገበው የዝላይ ጉዞ፣ ኢትዮጵያን ከሸማችነት ወደ አምራችነት፣ ከተከታይነት ወደ ግንባር ቀደምትነት እያሸጋገራት ይገኛል።
ኢትዮጵያ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ በዳታ እና በሮቦቲክስ ግንባር ቀደም ተዋናይ እየሆነች ነው። በአፍሪካ የመጀመሪያውን የAI ኢንስቲትዩት በማቋቋም እና በዓለም ሁለተኛ የሆነውን የAI ዩኒቨርሲቲ በመገንባት፣ የነገውን የዓለም የቴክኖሎጂ አቅጣጫ ከሚወስኑት ተርታ ተሰልፋለች።
ከዚህም አልፎ፣ ከግዙፉ የቦይንግ ኩባንያ ጋር በተደረገ ስምምነት የአውሮፕላን መለዋወጫዎችን በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመሯ፣ የኢትዮጵያን አቅም ወደ ላቀው የኤሮስፔስ ኢንዱስትሪ አሸጋግሯታል።
የዲጂታል መሠረተ ልማታችንም ቢሆን ከ41 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ባቀፈው የ"ፋይዳ" ዲጂታል መታወቂያ እና ሦስት ሚሊዮን ወጣቶችን አሰልጥኖ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ በሚያሰማራው የ"አምስት ሚሊዮን ኮደሮች" ንቅናቄ ጸንቶ እየተገነባ ነው።
ድሬዳዋን እና ገዳን የመሳሰሉ ልዩ የኢኮኖሚ ቀጠናዎች (SEZ) ከሎጂስቲክስ እና ከባቡር መስመር ጋር ተሣሥረው፣ የማምረት አቅማችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ አድርገውታል።
ከዚህም ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን ከሰው ልጆች ደኅንነት እና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ወደሚያቀናጀው ወደ አምስተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት በልበ ሙሉነት ተራምዳለች። የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦታችን 100 በመቶ ከታዳሽ ምንጮች (ውኃ፣ ንፋስ፣ ፀሐይ) መሆኑ፣ በዓለም ገበያ ተመራጭ የሆኑ "አረንጓዴ ምርቶችን" እንድናመርት አድርጎናል።
የነዳጅ ጥገኝነትን የሚሰብረው እና ከ100 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሥራ ያስገባው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች አብዮት፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥ እየተመረቱ ከተሞቻችንን ብሩህ፣ ዘመናዊ እና ስማርት የሚያደርጉት፣ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩና 5G ኔትዎርክ የሚያሰራጩት "ስማርት ፖሎች" የዚህ ዓረንጓዴ እና ዘመናዊ ጉዞ ሕያው ምስክሮች ናቸው።
ይህ እሳቤ እና ራዕይ መሬት የወረደ እና ፍሬ ያፈራ እንጂ በወረቀት ላይ የቀረ ምኞት አይደለም። በ"ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ የተገኘው የማክሮ-ኢኮኖሚ ስኬት ለዚህ ማሳያ ነው።
የፋብሪካዎቻችን የማምረት አቅም አጠቃቀም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 66.3 በመቶ ማደጉ፣ ምርት አቁመው ዝገት በልቷቸው የነበሩ 830 ፋብሪካዎች ዳግም ሕይወት ዘርተው ወደ ሥራ መመለሳቸው፣ እንዲሁም 325 አዳዲስ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸው አንገት ቀና የሚያደርግ አኩሪ ድል ነው።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 4.85 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት መቻላችን፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን በተግባር ያረጋገጠ ቁልፍ እርምጃ ነው።
የዘመናት የድህነት እና የሸማችነት ታሪካችንን ልንቀይር የምንችለው በዚህ የዝላይ ስልት እና የቴክኖሎጂ ጉዞ ብቻ ነው። ያለፈው ስብራት ቁጭት ፈጥሮብን የዛሬውን የሥራ መንፈስ ሊያቀጣጥለው ይገባል።
ዛሬ ላይ ሆነን የምንገነባው ማኑፋክቸሪንግ፣ የምናሠለጥነው የዲጂታል አቅም እና የምንዘረጋው አረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የቴክኖሎጂ እና የኢንዱስትሪ ማዕከል የማድረግ ታላቅ ራዕይ አካል ነው።
ተያይዘን ከሠራን፣ በፈጠራ ከታጠቅን እና ቴክኖሎጂን ከጉልበታችን ጋር ካዋሃድን፣ የማንደርስበት ከፍታ፣ የማንሰብረው የድህነት ማነቆ አይኖርም።
ኢትዮጵያ ታምርታለች፤ ትንሣኤዋም በልጆቿ እጅ እውን ሆኗል! ዳግም ወደኋላ አንመለስም፣ የጀመርነው የዝላይ ጉዞ ኢትዮጵያን በዓለም የኢንዱስትሪ ማማ ላይ እስክናሰፍር ድረስ በፍጥነት ይቀጥላል!
#EBC #Ethiopia #MadeInEthiopia #industry #leapfroging