ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ የተጠናቀቀውን ምዕራፍ አንድ ግንባታ ዛሬ በይፋ መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፣ የዚህ ፕሮጀክት መመረቅ አስተማማኝ እና ጠንካራ ኢኮኖሚን ለመገንባት በተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ውስጥ ተደማሪ እመርታ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመዲናዋ በአጠቃላይ በ93.9 ሄክታር መሬት ላይ ከሚያርፈው የፓርኩ አጠቃላይ ስፋት ውስጥ፣ የመጀመሪያው ምዕራፍ በ43 ሄክታር መሬት ላይ ተገንብቶ ዛሬ የተመረቀ ሲሆን፣ ይህም ለመካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞች ምቹ የንግድ ከባቢ ከመፍጠር ባሻገር በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች አዲስ የሥራ ዕድል የሚከፍት መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርኩ የሀገራችን አምራቾች አቅማቸውን በማጎልበት፣ ምርታማነታቸውን ማሳደግና ተወዳዳሪነታቸውን በመጨመር ለከተማችን፣ ለሀገራችንና ለቀጣናው የሚተርፉበትን ታላቅ ዕድል የያዘ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል ፓርኩ ተተኪ ምርቶችን በማምረት በአምራቾችና በሸማቾች መካከል ቀጥተኛና ቀልጣፋ የንግድ ትስስር የሚፈጥር ሲሆን፣ ምርቶችን ደግሞ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሀገራችንን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው አስታውቀዋል።