Search

ገላን ጉራ ኢንደስትሪያል ፓርክ፤ ምንና እንዴት?

ቅዳሜ ግንቦት 08, 2018 160

የታሪክ ድርሳናቶቻችንን ስንገልጥ ኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌት፣ በራሷ የምትተማመን የጀግንነት አምባ መሆኗን በኩራት እናነባለን። ይሁን እንጂ፣ ይህ አኩሪ ሀገራዊ ክብር በኢኮኖሚው ሚዛን ላይ ሲመዘን አንገት የሚያስደፋ ጥልቅ የቁጭት ስሜት ይፈጥርብናል።

የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ጸጋ፣ ለም መሬት፣ እና በቢሊዮን የሚቆጠር ጉልበት ያለው ታታሪ የሰው ኃይል ይዘን፤ ለዘመናት የውጭ ሀገራት የፋብሪካ ውጤቶች ማራገፊያ፣ የባዕዳን ምርት ሸማችና "አስመጪ" በሚል አሳዛኝ ስም ስንጠራ ኖረናል።

የገዛ የቆዳ ምርታችንን በሳንቲም ሸጠን፣ የተሰራውን ጫማ በዶላር ስንገዛ፤ የገዛ ጥጣችንን ወደ ውጭ ልከን፣ የተፈተለውን ልብስ በውድ ዋጋ ስንሸምት ዘመናትን አሳልፈናል። ወጣቶቻችን በሥራ አጥነት ሲንገላቱ፣ ፋብሪካዎቻችን በጥሬ ዕቃ እጥረት ሲቆሙ ማየት የዘወትር ትዕይንት ሆኖ ቆይቷል።

ይህ የታሪክ ስብራት ሊያበቃ፣ ይህ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ጥገኝነት ሊሰበር የግድ ይላል ዛሬ ላይ ይህንን የዘመናት ቁጭት ወደ ተግባራዊ ተስፋ፣ አስመጪነትን ወደ አምራችነትና ላኪነት ለመቀየር የተጀመረው ዐቢይ አብዮት አንዱና ዋነኛው ሕያው ማሳያ የገላን ጉራ ኢንደስትሪያል ፓርክ ነው።

የኢኮኖሚ ሽግግሩ ሕያው ምስክር የሆነው የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምንነትና ዝርዝር ገጽታ፤

ዓለም ላይ ታላላቅ የኢኮኖሚ ተዓምራቶች በአጋጣሚ የተፈጠሩ ሳይሆኑ፣ በጠንካራ የኢንዱስትሪ መሠረት ላይ የተገነቡ ናቸው። ደቡብ ኮሪያ ከጦርነት አመድ ስትነሳ የነደፈችው የኢንዱስትሪ ኮምፕሌክሶች ሥልት፣ እንዲሁም ሲንጋፖር ከትንሽ ወደብ ከተማነት ወደ ዓለም አቀፍ የንግድና የቴክኖሎጂ ማዕከልነት ስትለወጥ የተጠቀመችው ዘመናዊ የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ለዚህ ማሳያዎች ናቸው።

የነገዋን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመገንባት ቆርጣ የተነሳችው ኢትዮጵያም፣ ይህንን ስልት ወደ መሬት በማውረድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማካኝነት በቢሊዮኖች የሚቆጠር በጀት መድባ ያስገነባችው ግዙፍ ማዕከል ነውገላን ጉራ ኢንደስትሪያል ፓርክ።

ይህ ፓርክ በሀገራችን ታሪክ በሕንጻ ደረጃ የተሠራ የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ ፓርክ በመሆን አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። በመጀመሪያው ምዕራፍ (Lot-1 እና Lot-3) ግንባታ ብቻ 7 ቢሊየን ብር በላይ የፈሰሰበት ይህ ግዙፍ ማዕከል፣ 442 የማምረቻ ቦታዎችን አቅፏል።

ገላን ጉራ ዝም ብሎ የተገነባ የኮንክሪት ክምችት አይደለም፤ ይልቁንም ዘመናዊነትን የተላበሱ በርካታ አውታሮችን የያዘ ነው፡-

የተሟላ መሠረተ ልማት፡ ከዘመናዊ የማምረቻ ክፍሎች እስከ ምርት ማከማቻ ጎተራዎች፣ ከቢሮዎች እስከ ሰፊ የመመገቢያ አዳራሾች ያካተተ ነው።

አስተማማኝ ኃይልና ውኃ፡ ራሱን የቻለ የከርሰ ምድር ውኃ ምንጭ ያለው ሲሆን፣ 24 ሰዓት የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንዲኖርና የኃይል መቋረጥ እንዳይከሰት 1250KVA ኃይል ማመንጨት የሚችሉ ትራንስፎርመሮች እና ግዙፍ የነዳጅ ታንከሮች ተገጥመውለታል።

ሁለንተናዊ አገልግሎት፡ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ እንድትራመድ የሚያግዙ የምርምርና ጥናት እናቶች በስራቸው ላይ ሙሉ ትኩረት እንዲያደርጉ የሚያስችል የህጻናት ማቆያፈጣን የኢንተርኔት መስመር፣ እንዲሁም ለምርትና ለሰው ደኅንነት ዘብ የቆሙ ዘመናዊ የደኅንነት መጠበቂያ መሣሪያዎች ተሟልተውለታል።

በፓርኩ ውስጥ 48 ደረጃቸውን የጠበቁ የብረታ ብረት፣ የእንጨት ውጤቶች እና የኬሚካል ፋብሪካዎች፤ እንዲሁም 68 ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የቆዳ፣ የጨርቃ ጨርቅ እና የፕላስቲክ ኢንዱስትሪዎች ምርቶቻቸውን በጥራት እያዘጋጁ ለገበያ ያቀርባሉ።

የገላን ጉራ ኢንደስትሪያል ፓርክ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዴት?

ይህ ማዕከል ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚሰጠው ትርጉም ቀላል አይደለም፤ የሕልውና እና የዕድገት መሠረት ነው። 2022 (እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር) ሀገራችንን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተነደፈውን የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ለማሳካት ከሚጫወታቸው ወሳኝ ሚናዎች መካከል ዋነኞቹ የሚከተሉት ናቸው፡-

1. የአምራቾች የጋራ ኃይልና የኢንቨስትመንት ስበት ፓርኩ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራቾችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ የኢንዱስትሪ ክላስተር እንዲፈጥሩ ያደርጋል። ይህ መዋቅር የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍን በቀላሉ ለማድረስ፣ እንዲሁም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ምቹና ማራኪ የኢንቨስትመንት ዕድልን ለመፍጠር ያስችላል። አምራቾች ተበታትነው ከሚገጥማቸው የግብዓትና የሎጂስቲክስ ፈተና ወጥተው፣ በአንድ ጣሪያ ስር በጋራ ተደጋግፈው እንዲያድጉ ያደርጋል።

2. የምርት ወጪን በእጅጉ መቀነስ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ትልቁ ማነቆ የመሠረተ ልማት አለመሟላት እና ወጪ ነው። ገላን ጉራ ፓርክ አስተማማኝ የውኃ፣ የኤሌክትሪክና የትራንስፖርት አገልግሎትን በተደራጀ መንገድ በማቅረቡ፣ ፋብሪካዎች ለነዚህ አገልግሎቶች የሚያወጡትን ከፍተኛ ወጪና ጊዜ ይቆጥባል። የቆጠበው ወጪና ጊዜ ምርቶቻቸውን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ ለማቅረብ ቁልፍ መሣሪያ ይሆናቸዋል።

3. የገበያ ትስስር እና የምርት ጥራት ማሻሻል ማምረት ብቻውን በቂ አይደለም፤ ገበያ ማግኘት እና ሸማችን ማሳመን ወሳኝ ነው። ፓርኩ አምራቾች ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለሸማቾችና ለዓለም አቀፍ ገዢዎች የሚያስተዋውቁበት ሰፊ የኤግዚቢሽንና የገበያ ማሳያ ቦታዎችን አዘጋጅቷል። ፋብሪካዎች በጋራ መሠረተ ልማት መጠቀማቸውና በምርምር ማዕከላቱ በኩል የዕውቀት ልውውጥ ማድረጋቸው፣ የምርትና አገልግሎት ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ አሻሽሎ የውጭ ምንዛሬን ለማዳንና ለማስገኘት ያስችላል።

4. የከተማ ገጽታ ግንባታ እና አረንጓዴ ልማት የኢንዱስትሪ ልማት ማለት የቆሻሻ ክምችት እና የአካባቢ ብክለት ማለት አይደለም። ገላን ጉራ ይህንን የተሳሳተ ትርክት የሚሰብር እና አዲስ የከተማ ልማት ፍልስፍናን የሚያስተዋውቅ ነው። ማዕከሉ ዘመናዊ የፍሳሽ ማጣሪያ፣ የድሬኔጅ ሥርዓት፣ ዘመናዊ የቆሻሻ አወጋገድ እና ሰፊ የአረንጓዴ ቦታዎች አገልግሎቶችን አሟልቶ የያዘ ነው። በዚህም የአዲስ አበባን የኢኮኖሚ ማዕከልነት ከማጠናከር ባለፈ፣ የከተማዋን ገጽታ የሚያሳምርና ለቀጣዩ ትውልድ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃን የሚያረጋግጥ ነው።

ወደፊት የምንራመድበት አዲስ ጎዳና

የገላን ጉራ ኢንደስትሪያል ፓርክ የብረትና የሲሚንቶ ክምችት አይደለም፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ትንሣኤ ሕያው ምስክር ነው። ለዘመናት በደጃፋችን ላይ ተቆልሎ የነበረውን፣ "አንችልም" የሚለውን የጥገኝነት አስተሳሰብ ሰብረን፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ኢንዱስትሪዎችን በገዛ ሀገራችን ምድር በተግባር መገንባት እንደምንችል ያረጋገጥንበት ዐቢይ ብሔራዊ ድል ነው።

ይህ ማዕከል የሥራ አጡን ወጣት እንባ የሚያብስ፣ የባለሀብቱን ራዕይ ወደ ዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያሰፋ፣ እና ሀገራዊ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን በዘላቂነት የሚፈታ ሞተር ነው። የተንጠባጠቡትን የልማት ጅማሬዎቻችንን ወደ አንድ ጠንካራ ወንዝ በመቀየር፣ ኢትዮጵያን ከአስመጪነት ወደ ላኪነት፣ ከሸማችነት ወደ አምራችነት የሚያሸጋግራት ሰፊ ድልድይ ነው።

በመሆኑም፣ ይህ ማዕከል የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ኩራትና የለውጥ ማነቃቂያ ሊሆን ይገባል። ያለፈው ታሪካችንን በቁጭት እያሰብን፣ የነገዋን የበለጸገች፣ ሉዓላዊነቷ በኢኮኖሚዋ የተረጋገጠች ሀገር ለመገንባት በዚህ አዲስ የኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል። የገላን ጉራ ብርሃን የሀገራችንን የኢኮኖሚ ሰማይ በደመቀ ሁኔታ ማብራት ጀምሯል፤ ይህ ጅማሬ የትውልድ ቅርስ ሆኖ ዘላቂ የኢኮኖሚ ነፃነታችንን እስከምናውጅ ድረስ፣ የለውጡ ጉዞ በፍጥነትና በጽናት ይቀጥላል

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ