ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲሱ የገላን ጉራ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአካባቢው የመጣውን ሁለንተናዊ ለውጥና የኢትዮጵያን የወደፊት የኢንዱስትሪ አቅጣጫ አስመልክተው ጥልቅ መልእክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ መኪና የማይደርስበትና ሰው የማይረግጠው ገጠር የነበረው ይህ አካባቢ፣ ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለውበት፣ ውብ መንገዶችና መብራቶች ተሟልተውለት፣ እንዲሁም የኢንዱስትሪና የቤት ግንባታዎች ተከናውነውለት ከከተማዋ ማዕከል ይበልጥ የተሻለ ዘመናዊ ሰፈር መሆኑን ገልጸዋል። ይህ ስኬት ቦሌ ለሚን፣ ጎሮን፣ ሲኤምሲንና ቦሌን በማገናኘት አዲስ ከተማና አዲስ መልክ የፈጠረ በመሆኑ ፈጣሪን እንደሚያመሰግኑ ተናግረዋል።
በንግግራቸው ወቅት ቀደም ሲል በከፍተኛ ብድር የተገነባውን የሀዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ተሞክሮ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በወቅቱ ሰፊ ሼዶች ተገንብተው የውጭ ባለሀብቶች መጥተው የነበረ ቢሆንም፣ ችግር ሲያጋጥም ሰማኒያና ዘጠና በመቶ የሚሆነውን ጥለውት መሄዳቸውንና ያሉትም ታክስና የተለያዩ ምሬቶችን እንደሚያነሱ አስታውሰዋል።
በአንጻሩ ዛሬ በገላን ጉራ ያዩአቸው ወጣቶች ግን የዛሬ አራትና አምስት ዓመት ሥራ ያልነበራቸው፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ዛሬ እስከ 60 ሰው የቀጠሩና ነገ በሺዎች ለመቅጠር ተስፋ የሰነቁ መሆናቸውን በኩራት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የወደፊት የኢንዱስትሪ ባለቤቶች (ኢንዱስትሪያሊስቶች) የሚፈልቁት ከእነዚህ የሀገር ውስጥ ወጣቶች መካከል መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ወጣቶች በፓርኩ ውስጥ ለግብርና የሚሆን ፓምፕ፣ የወርቅ ማምረቻ، የመኖና የብሎኬት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ማምረት መጀመራቸውንና ፋብሪካን ማምረት የሚችሉ ወጣቶችን ማገዝ ፍሬው የሚባረክ መሆኑን አብራርተዋል።
የመንግሥት ፍላጎትና ሕልም ከድህነት የተለቀቀች ሀገር መፍጠርና የሚሠራ ትውልድን መርዳት እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ይህ ዜጋ ክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ አማራ ወይም ኦሮሞ ሳይባል ኢትዮጵያዊ በሙሉ ራሱን ችሎ እንደ ሶማሊያ፣ ኬንያና ዩጋንዳ ያሉ የጎረቤት ሀገራት ወንድሞችን ማገዝ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ መሻታቸውን ገልጸዋል።
ልማት ደሀንና አርሶ አደርን ሳይጥል፣ ሕይወታቸውን በሚያሻሽልና ባቀፈ መልኩ መሠራት እንዳለበት ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአዲስ አበባ ቤቶች ፈርሰዋል የሚባለውን ወሬ ከጊዜያዊ ፍላጎትና ከፖለቲካ ወጣ ብሎ ማየት እንደሚያስፈልግና ካልሠራንና ላባችን ካልተንጠባጠበ ለውጥ እንደማይመጣ አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም በሀገሪቱ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ የሚታየውን የሥራ አጥነት ወሬና በተግባር ያለውን የሥራ ኃይል እጥረት በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንደ ወንጪ ቤተክርስቲያን ግንባታ፣ ጅማ እና ስኳር ፋብሪካዎች ባሉባቸው ቦታዎች የሠራተኛ እጥረት በመኖሩ ምክንያት ከሌሎች ሀገራት ጭምር ሠራተኞች እየመጡ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያውያን ሊነቁና በሥራ ላይ ሊተጉ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ኢትዮጵያ በደፈናው አፍሪካ 10.2 በመቶ የምታድግ ብቸኛ ሀገር መሆኗን መናገራቸውን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንን ዕድገት ለማፋጠን ዜጎች በእምነት፣ በቋንቋና በጾታ ሳይከፋፈሉ ሊከባበሩና ሊዋደዱ እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል።
እየተሠሩ ባሉ የልማት ሥራዎች ውስጥ ሌብነት እንደ አረም እንዳይኖር ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባና ሁሉንም አቅፎ በንፁህ ልቦና መሥራት ከተቻለ የኢትዮጵያ ብልፅግና እውን ሆኖ ልጆቻችን በፍጹም እንደማይለምኑ እምነታቸውን ገልጸዋል።