Search

ፈተናን ወደ ዕድል፣ በፅናትና በትጋት መሻገር ፡- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተምሳሌታዊ አመራር

ረቡዕ መጋቢት 23, 2018 510

በኢትዮጵያ ረጅም፣ ውስብስብ እና ውጣ ውረድ በበዛበት የታሪክ ጉዞ ውስጥ፣ ያለፈውን ታሪክ ከዛሬና ከነገ ጋር አስማምተው፣ ሀገራዊ ህልውናን ከዘመናዊ ስልጣኔ ጋር አቆራኝተው፣ የህዝብን ስነ-ልቦናዊ ስብራት ጠግነው፣ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈቱ ስምንት ዓመታት ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ በእርግጥም ያለፉት ስምንት ዓመታት የለውጥ ጉዞ፣ ኢትዮጵያ ከነበረችበት ጥልቅ የፖለቲካ ቀውስ፣ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል፣ የታሪክ እዳ፣ እና የመነጣጠል ስጋት ወጥታ ወደ አዲስ የዕድገት ምህዋር የተሸጋገረችበት ወቅት መሆኑ በታሪክ ድርሳናት በጉልህ የሚሰነድ ትውልድ የሚያወሳው የታሪክ መታጠፊያ ነው።

ይህ የታሪክ አጋጣሚ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ወደ ስልጣን መምጣት እውን የሆነና፣ ይህችን ሀገር በጥልቀት በመውደድና ለሀገር ክብር በመቅናት የተፈጠሩ የዘመናት ቁጭቶች ወደ ተጨባጭ ተግባር እንዲቀየሩ ሰፊ ዕድል የተገኘበት ወቅት ነው፡፡ እርሳቸው ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር የቀጣይ ዘመናትን የለውጥ ፍኖተ ካርታ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ከመሆኑም ባሻገር፣ ዜጎች በሀገራቸው ተስፋ እንዲሰንቁ ትልቅ የስነ-ልቦና መነቃቃትን የፈጠረ ነበር። የሳቸው አመራር ተራ አስተዳደራዊ ሽግግር ሳይሆን፣ ኢትዮጵያን እንደ ሀገረ-መንግስት (Nation-State) ጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም የተደረገ ስር ነቀል የተቋማትና የአስተሳሰብ ሪፎርም ነው።

የመደመር ፍልስፍና፡ የስነ-ልቦናዊ መሰረትና የተምሳሌታዊ አመራር ማሳያ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስኬት በዘፈቀደ፣ በአጋጣሚ ወይም በውጭ ሃይሎች ግፊት የተገኘ ሳይሆን፣ "መደመር" በተሰኘው ሀገር በቀል ፍልስፍና እና በተግባራዊ መሪነት (ገቢር ነበብነት/Pragmatism) ላይ የተመሰረተ ነው። መደመር ማለት ባለፉት ዘመናት የተገነቡ አወንታዊ የሀገር ወረቶችን እና እሴቶችን ጠብቆ ማቆየት፣ በታሪክ ሂደት የታዩ ስህተቶችን እና ስብራቶችን ደግሞ በቅንነትና በዕውቀት ማረም፣ እንዲሁም ለዘመኑና ለወደፊቱ የሚያስፈልጉ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ጨምሮ ሀገርን ወደ ላቀ ከፍታ የማሸጋገር የረቀቀ የአመራር ጥበብ ነው።

በእሳቸው መሪነት ኢትዮጵያ ከውጭ የሚመጡ ርዕዮተ-ዓለሞችን ያለአግባብ ተቀብሎ የመተግበርን ኋላቀርና ተቸካይ ፖለቲካዊ ባህል ሰብራለች። ሁሉንም አፍርሶ ከዜሮ የመጀመርን አውዳሚ ፖለቲካዊ ልምድ በመተው፣ በትውልዶች መካከል የልማትና የታሪክ ቅብብሎሽ እንዲኖር አስችለዋል። ይልቁንም፣ ጊዜያዊ ግቦችን ሳይሆን ዘላቂነት ያላቸውን መፍትሄዎች በማመንጨት ኢትዮጵያ በፈጣን የዝላይ መንገድ እንድትጓዝ አድርገዋል። ይህ አመራር በተግባር የተፈተነ፣ ፈተናዎችን ወደ ዕድል የሚቀይር፣ እና "የማይቻል" የሚባለውን ትርክት የሰበረ ነው።

የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማሲ እና የፖለቲካ ሪፎርም፡ የዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና የውስጥ ዴሞክራሲ ግንባታ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የውስጥ ፖለቲካዊ ሪፎርም ኢትዮጵያን ከተቆለፈባት ሳጥን አውጥቶ በዓለም አደባባይ ደረቷን ነፍታ፣አንገቷን ቀና አድርጋ ጥቅሟን አስከብራ እንድትቆም ያደረገ ነው:-

·       የፖለቲካ ምህዳርና ተቋማዊ ሪፎርም፡ ፖለቲካው ከጠላትነት ወደ ፉክክርና ትብብር እንዲሸጋገር ተደርጓል። የዴሞክራሲ ተቋማት (እንደ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን) ከመንግሥት ጫና እና ጣልቃ ገብነት ውጭ ነጻና ገለልተኛ ሆነው እንዲደራጁ ተደርጓል። ከገዥው ፓርቲ የተለየ እይታ ያላቸው አደረጃጀቶች በተፎካካሪነት እንጂ በጠላትነት የማይታዩበት፣ ብሎም በአመራርነት ቦታ ጭምር ተመድበው ሀገር የሚያገለግሉበት አዲስ ባህል ተፈጥሯል።

·     የብሪክስ (BRICS) አባልነት፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አርቆ አሳቢ፣ የማይበገር እና ስልታዊ የዲፕሎማሲ ተጋድሎ ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) ሙሉ አባል መሆን ችላለች። 40 በላይ ሀገራት ጥያቄ ባቀረቡበትና ከፍተኛ ፉክክር በነበረበት ዓለም አቀፍ መድረክ ኢትዮጵያ ተመርጣ መግባቷ የኢትዮጵያን የጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና የወደፊት የኢኮኖሚ አቅም በግልጽ ያሳየ ነው። ይህ ድል ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የሃይል ሚዛን ውስጥ ያላትን ስትራቴጂካዊ ቦታ ያረጋገጠ ነው።

·      የህዳሴ ግድብ እና የውሃ ዲፕሎማሲ፡ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን፣ ዛቻዎችንና ውስብስብ ሴራዎችን በጥበብ በመመከት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን (GERD) ከስብራት አውጥተው፣ የተጓተቱ ኮንትራቶችን አስተካክለው፣ ግድቡ ውሃ ይዞ ሃይል ወደማመንጨት እንዲሸጋገር አድርገውታል። ጉዳዩ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ሲወሰድ "ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" በሚል መርህ ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ በማድረግ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ተቀዳጅተዋል። ከዚህም ባለፈ አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው የአባይ ወንዝ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) በህጋዊ መንገድ ወደ ሥራ እንዲገባ በማድረግ ታሪካዊ የመሪነት ሚናቸውን በተግባር አረጋግጠዋል።

·    ፍትሐዊ የባሕር በር ጥያቄ፡ ለሶስት አስርት አመታት ታፍኖ፣ እንደ ነውር ተቆጥሮ የኖረውን የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከድብቅነት አውጥተው ዓለም አቀፍ አጀንዳ እና እውቅና እንዲያገኝ አድርገዋል። ይህ 130 ሚሊዮን ህዝብ ህልውና ጥያቄ በድፍረት በማንሳት ከፊት ለፊት በመቆም  ለዓለም አሳውቀዋል።

·    ቀጣናዊ ሰላም አውራነት፡ "ቅድሚያ ለጎረቤት" በሚል የውጭ ግንኙነት መርህ የሱዳንን የሽግግር መንግስት በማግባባት በኩል፣ በደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት፣ እንዲሁም በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ግንባር ቀደም አሸማጋይና የሰላም አስከባሪ በመሆን የኢትዮጵያን ቀጣናዊ የመሪነት ሚና አጽንተዋል። የውጭ ፖሊሲው ሀገራዊ ጥቅምን ከዜጎች ክብር ጋር አቆራኝቶ የሚሰራ ነው።

የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የማክሮ-ኢኮኖሚ መረጋጋት፡ የቁርጠኝነትና የስኬት ማሳያዎች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስልጣን ሲረከቡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በከፍተኛ የውጭ ዕዳ ጫና፣ በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በመዋቅራዊ ብልሽት፣ እና በሙስና በተተበተቡ የፕሮጀክቶች መጓተት ክፉኛ ታሞ ነበር። ይህንን መሰረታዊ ችግር በመገንዘብ "ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ" (Homegrown Economic Reform 1.0 እና 2.0) ቀርጸው ወደ ፈጣን ተግባር ገብተዋል። በዚህም የተገኙት የኢኮኖሚ ማመላከቻ ውጤቶች አስደናቂ ናቸው:-

·     የኢኮኖሚ ዕድገት፡ ዓለም አቀፍ (እንደ ኮቪድ-19 እና ጦርነቶች) እንዲሁም ሀገራዊ ፈተናዎችን በጽናት በመቋቋም ባለፉት አምስት ዓመታት ኢኮኖሚው በአማካኝ 7.45 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን፣ በቅርቡ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ባወጣው ሪፖርት መሰረት ደግሞ ዕድገቱ ወደ 9.2 በመቶ ከፍ ማለቱ ተረጋግጧል። ይህ ማመላከቻ ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት ካላቸው ጥቂት ሀገራት ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል።

·       ዕዳን የማቃለል ታሪካዊ ተጋድሎ፡ ለቀጣዩ ትውልድ የዕዳ ሸክምን ላለማውረስ በወሰዱት የቁርጠኝነት እርምጃ 2010 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ብቻ 12.7 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ መክፈል ተችሏል። በተጨማሪም መንግስት ባደረገው ስኬታማ የፋይናንስ ዲፕሎማሲ 3.5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም የተደረገው ስኬታማ ድርድር ኢትዮጵያን ከከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ታድጓታል።

·       የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና ንግድ፡ ኢኮኖሚውን ለግሉ ዘርፍ ክፍት በማድረግ፣ ቴሌኮምና ፋይናንስን ጨምሮ ዝግ የነበሩ ዘርፎችን በማላቀቅ ባለፉት አምስት ዓመታት 18.6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት (FDI) መሳብ ተችሏል። የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) ገቢ ከለውጡ በፊት ከነበረበት 3.62 ቢሊዮን ዶላር አድጎ 8.3 ቢሊዮን ዶላር መድረስ ችሏል። ከዚህም ጋር በተያያዘ የውጭ ሀገር ሐዋላ (Remittance) ፍሰት 7.06 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ የሪፎርሙ ትልቅ ስኬት ነው።

·       የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ገቢ አሰባሰብ፡ 2014 እስከ 2017 ባሉት አራት ዓመታት ብቻ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ህጋዊ የስራ ስምሪት 15 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። የሀገሪቱ የገቢ አሰባሰብ ከስምንት ዓመት በፊት ከነበረበት 170 ቢሊዮን ብር በአሁኑ ወቅት ወደ 1 ትሪሊዮን ብር ማደጉ ኢኮኖሚው ከዕርዳታ ጥገኝነት ወጥቶ በራስ አቅም ላይ መቆም መጀመሩን ያሳያል።

ግብርና እና አረንጓዴ አብዮት፡ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ስትራቴጂ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት አንዱ ትልቅ መለያ የግብርናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እና የአካባቢ ጥበቃ ቁርጠኝነት ነው።

·   የስንዴ እና የግብርና አብዮት፡ የግብርናውን ባህል ከዝናብ ጥገኝነት እና ከኋላቀር አሰራር በማላቀቅ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በስፋት በማስተዋወቅ ታላቅ ስኬት ተመዝግቧል። ጠቅላላ የስንዴ ምርት 59.16 ሚሊዮን ኩንታል በማደግ 280 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል። በዚህም ኢትዮጵያ ስንዴ ከውጭ ማስመጣት አቁማ ራሷን ከመቻልም አልፋ ወደ ውጭ መላክ የቻለችበት የታሪክ እጥፋት ላይ ትገኛለች። የቡና ምርትም ወደ 11.4 ሚሊዮን ኩንታል ማደጉ፣ እንዲሁም በስድስት ወራት ብቻ 999 ሚሊዮን ኩንታል ሰብል መመረቱ የዘርፉን ትራንስፎርሜሽን ያሳያል።

·    የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ (Green Legacy) የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለመመለስ፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተወሰደው ታሪካዊ እርምጃ ባለፉት አመታት 48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። በዚህም የሀገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 23.6 በመቶ ከፍ ብሏል። ይህ ታላቅ የዜጎች ንቅናቄ ስራ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን ያገኘ ሲሆን፣ ለዚህም ሲባል የዓለም የምግብ ድርጅት (FAO) "አግሪኮላ ሜዳልያ" (Agricola Medal) ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አበርክቶላቸዋል። እንዲሁም ኢትዮጵያ "ዘላቂ የደን ልማት" FAO ሽልማትን ተቀብላለች።

የገበታ ፕሮጀክቶች፣ የከተማ ውበት እና የመሰረተ ልማት ትራንስፎርሜሽን

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የአመራር ፍልስፍና እና "የሚቻልበትን መንገድ የመፍጠር" እይታ በጉልህ ከሚታይባቸው ስራዎች መካከል "የገበታ ፕሮጀክቶች" እና የከተማ ኮሪደር ልማቶች በዋናነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ፕሮጀክቶች የመንግስትን መደበኛ በጀት ሳይነኩ፣ ህዝብን፣ ባለሃብቱን እና ተቋማትን በማስተባበር የተሰሩ አስደናቂ የአመራር ብቃት ማሳያዎች ናቸው። እነዚህ ስራዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውን የተጓተተ የፕሮጀክት አስተዳደር ባህል በመስበር በፍጥነት፣ በጥራት፣ እና በከፍተኛ የውበት ደረጃ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንደሚቻል ያረጋገጡ ተቋማዊ ትምህርት ቤቶች ናቸው:-

·     ገበታ ለሸገር (Dine for Sheger) አዲስ አበባን ስሟን የሚመጥን ገጽታ እንድትላበስ ለማድረግ የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት፣ ለዘመናት ተረስተው የነበሩ የከተማዋን ክፍሎች ወደ ውብ የቱሪስት መዳረሻነት ቀይሯቸዋል። ወዳጅነት ፓርክ (Friendship Park) የአንድነት ፓርክ (Unity Park) እና የእንጦጦ ፓርክ ግንባታዎች ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለቱሪስቶች ማራኪ አድርገዋታል። በተለይ የእንጦጦ ፓርክ ግንባታ ቀድሞ ማንም ዞር ብሎ የማያየውን ተራራ ወደ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የመዝናኛ፣ የስፖርት እና የቱሪዝም ማዕከልነት የለወጠ የፈጠራ ስራ ነው።

·       ገበታ ለሀገር (Dine for Nation) ይህ ፕሮጀክት ከዋና ከተማዋ ወጥቶ በክልሎች ያሉ የተፈጥሮ ጸጋዎችን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለመቀየር ያለመ ነው። በዚህም የተገነቡት የወንጪ ሃይቅ ቱሪዝም መንደር፣ በደቡብ ክልል የተገነባው አስደናቂው ሃላላ ኬላ ሪዞርት፣ እና በአማራ ክልል የተገነባው ጎርጎራ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ፣ የታሪክ እና የባህል ጸጋ ወደ ገቢ ማስገኛነት የለወጡ ናቸው።

·       ገበታ ለትውልድ (Dine for Generation) የዚህ ዙር ፕሮጀክቶች ደግሞ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ ሃብት ለቀጣዩ ትውልድ በሚተርፍ መልኩ ለማልማት ያለሙ ናቸው። በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተገነቡ ያሉ ዘመናዊ መዳረሻዎች የቱሪዝም ዘርፉን የጀርባ አጥንት እያጠናከሩት ይገኛሉ።

·     የመንገድ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፡ በአዲስ አበባ የተጀመረውና አሁን ወደ ተለያዩ የክልል ከተሞች የተስፋፋው የኮሪደር ልማት፣ ከተሞችን ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ለንግድ ስራ አመቺ እና ከብክለት የጸዱ (Smart Cities) ለማድረግ ያለመ ነው። የመንገድ ማስፋፋትን፣ የእግረኛ መንገዶችን፣ የብስክሌት ሌኖችን፣ የመዝናኛ ስፍራዎችን እና ዘመናዊ የመብራት ስርአቶችን ያካተተው ይህ ፕሮጀክት፣ የከተማ ነዋሪውን የኑሮ ጥራት በከፍተኛ ደረጃ አሻሽሏል።

·       በተጨማሪም በቢሾፍቱ አካባቢ እየተገነባ ያለውና በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው አዲሱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከልነቷን ለዘመናት የሚያጸናላት ታላቅ ራዕይ ነው።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እና ዘመናዊ አሰራር

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮያን ከኋላቀር አሰራር አላቅቀው ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ፍጥነት ጋር ለማራመድ በርካታ እርምጃዎችን ወስደዋል።

·   "ፋይዳ" (Fayda) ብሄራዊ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮጀክት፡ ለዜጎች የተቀናጀ፣ ዘመናዊ እና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት፣ እስካሁን 27 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን መመዝገብ ችሏል።

·       ዲጂታል ኢኮኖሚ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፡ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱ በአንድ በጀት ዓመት ብቻ 16 ትሪሊዮን ብር የግብይት ልውውጥ ማስተናገድ መቻሉ ዘርፉ ያለበትን የእድገት ፍጥነት ያሳያል። በተጨማሪም የአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነው የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ኢንስቲትዩት መመስረት፣ ኢትዮጵያን በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከአለም ጋር እንድትወዳደር የሚያስችላት ቁልፍ የስትራቴጂ አካል ነው።

መደምደሚያ እና የቀጣይ ጉዞ እይታ

ያለፉት ስምንት ዓመታት የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞዎች በውስጥ እና በውጭ ፈተናዎች፣ በትርምሶች እና በጫናዎች የታጀቡ ቢሆኑም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ጥበብ የተሞላበት፣ ቁርጠኛና ፈጠራ የታከለበት መሪነት የተመዘገቡት ስኬቶች የታሪክ አቅጣጫን በእጅጉ የቀየሩ ናቸው።

ከፈራረሰና በዕዳ ከተተበተበ ኢኮኖሚ ወደ 9.2% ዕድገት፤ ከድርቅና መራቆት ስጋት ወደ 48 ቢሊዮን ችግኞች እና የምግብ ሉዓላዊነት፤ ከተዘጉና ከተጠረጠሩ የዲፕሎማሲ በሮች ወደ ብሪክስ (BRICS) አባልነት፤ እንዲሁም ከተረሱ ጫካዎችና ቆሻሻ ስፍራዎች ወደ አለም አቀፍ የገበታ ፕሮጀክቶችና የቱሪስት መዳረሻዎች የተደረገው አስደናቂ የዝላይ ሽግግር የመሪውን ጥልቅ ራዕይ፣ የላቀ የህዝብ አስተባባሪነት እና አመርቂ የአፈፃፀም ብቃት በተግባር ያረጋግጣል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/ኢትዮጵያን ከነበረችበት የውድቀትና የመበታተን ስጋት አውጥተው፣ የተበታተኑ አቅሞቿን በማስተባበር ወደ ብልፅግና ምህዋር ያስገቡ፣ የማይቻለውን የሚቻል መሆኑን በተግባር ያሳዩ፣ እና ለትውልድ የሚተርፍ ጠንካራ የሀገረ-መንግስት መሰረት የጣሉ ተምሳሌታዊ መሪ ናቸው። "መደመር" ፍልስፍናቸው እና በተግባር ያስመዘገቧቸው ድንቅ ውጤቶች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካም እንደ አዲስ የህዳሴ ሞዴል የሚጠቀሱ ናቸው። ወደፊትም ይህንን የለውጥ ጉዞ በማስቀጠል፣ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የኢኮኖሚ፣ የዲፕሎማሲ፣ የቴክኖሎጂ እና የፖለቲካ ማማ ላይ የማውጣት ራዕይ በተሳካ ሁኔታ እንደሚቀጥል፣ የመሪው ስብዕና፣ ማገር የሌለው ፅናት እና ለሀገር ያላቸው ጥልቅ ፍቅር ሕያው ማረጋገጫ ነው።

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ