ኢትዮጵያ በዓለማችን ጥቂት ሀገራት ብቻ ወደሚገኙበት እና በከፍተኛ የቴክኖሎጂ ብቃት በሚታወቀው የኑክሌር ኃይል ባለቤቶች ክለብ ለመቀላቀል እና የኢነርጂ ታሪኳን ዳግም ለመጻፍ የሚያስችላትን ግዙፍ ስምምነት ተፈራርማለች።
ይህ ታሪካዊ እርምጃ የሀገራችንን የኢነርጂ ሉዓላዊነት የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ፣ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና አዲስ የኃይል ሚዛን የሚፈጥር እንደሆነ ታምኖበታል።

የኢትዮጵያ የኑክሌር ኢነርጂ ኮሚሽን ከሩሲያው የኑክሌር ቴክኖሎጂ ግዙፍ ተቋም ሮሳቶም (Rosatom) ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን አዲስ የመንገድ ካርታ በይፋ መፈረሙ፣ ሀገራችን ወደ ኑክሌር ኢነርጂ ዘመን ለመሸጋገር ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት ለዓለም ያሳየችበት ክስተት ሆኗል።
የፈርስት ፖስት አድናቆት እና የኢትዮጵያ ግዙፍ ዕቅድ
ታዋቂው ዓለም አቀፍ የዜና ተቋም ፈርስት ፖስት (First Post) ይህንን የኢትዮጵያ ዝላይ በታላቅ አድናቆት የዘገበው ሲሆን፣ ስምምነቱ ኢትዮጵያ የኑክሌር መሠረተ ልማቶችን እንድትገነባ፣ የቴክኒክ ድጋፍ እንድታገኝ እና የሰው ኃይሏን በዘመናዊ መንገድ እንድታሠለጥን የሚያስችል መዋቅራዊ ዕቅድ የያዘ መሆኑን አብራርቷል።
ይህ እርምጃ ኢትዮጵያ የኑክሌር ኃይል ለመገንባት የያዘችውን የረጅም ጊዜ ሕልም ወደ ተግባር ምዕራፍ የሚያሸጋግር ታሪካዊ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።
የፈርስት ፖስት ተንታኝ እንደምትለው፣ ኢትዮጵያ በ30 ቢሊዮን ዶላር የምትገነባው የኑክሌር ፕሮጀክት ለምታከናውነው ሀገራዊ የልማት ፕሮግራም እንደ ዋነኛ የጀርባ አጥንት የሚቆጠር እና የኢኮኖሚ ገጽታዋን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ነው።
ከውኃ ጥገኝነት ወደ ኑክሌር አስተማማኝነት
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት 90 በመቶ የሚሆነው በውኃ ኃይል ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ በዝናብ መቆራረጥ እና በወንዝ የውኃ መጠን መለዋወጥ ምክንያት የሚፈጠረውን ስጋት ለመቀነስ የኑክሌር ኢነርጂ እንደ አስተማማኝ አማራጭ ቀርቧል።
እ.አ.አ ከ2032 እስከ 2034 ባሉት ዓመታት ውስጥ እያንዳንዳቸው 1 ሺህ 200 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችሉ ሁለት ግዙፍ የኑክሌር ኃይል ማብላያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱ በፈርስት ፖስት ዘገባ ላይ ተመላክቷል።
በየዓመቱ በ20 በመቶ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት እና ለግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንዲሁም ለከባድ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች የማያቋርጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የኑክሌር ቴክኖሎጂ መግባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ሆኗል።
የተቀናጀ የልማት ራዕይ እና የወደፊት ተስፋ
የኢትዮጵያ የኑክሌር ጉዞ ለብቻው የቆመ ሳይሆን፣ ከአዲሱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ ከነዳጅ ማጣሪያ እና ከተፈጥሮ ጋዝ ፋሲሊቲዎች ግንባታ ጋር የተቆራኘ ግዙፍ ብሔራዊ ዕቅድ አካል ነው።
ሩሲያ በቴክኖሎጂ እና በሰው ኃይል ሥልጠና የምታደርገው ድጋፍም ኢትዮጵያ በዘርፉ ራሷን የቻለች ባለሙያ ሀገር እንድትሆን ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
ኢትዮጵያ ከነፋስ እና ከውኃ በሚገኝ ታዳሽ ኃይል ላይ ብቻ ተወስኖ የመቅረት ፍላጎት እንደሌላት የጠቀሰችው የፈርስት ፖስት ተንታኝ፣ ይልቁንም በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የኑክሌር ኃይል ቁንጮ በመሆን የኢነርጂ ነጻነቷን ለማወጅ ተግታ እየሠራች እንደምትገኝ አረጋግጣለች።
ምንም እንኳ የኑክሌር ግንባታ ከፍተኛ ወጪ እና ረጅም ጊዜ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ለሀገራዊ ኢንዱስትሪ ዕድገት እና ለቀጣዩ ትውልድ የሚኖረው ፋይዳ ከምንም በላይ ሚዛን የሚደፋ በመሆኑ ሀገራችን ይህንን ታላቅ የቴክኖሎጂ ሽግግር በድል ለመወጣት ጉዞዋን በይፋ ጀምራለች።
ይህ ታላቅ ጉዞ ኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ እና የኃይል ማዕከል በማድረግ ለዜጎች ሁሉ አዲስ የብልጽግና ተስፋን ሰንቋል።
በለሚ ታደሰ
#Ethiopia #NuclearEnergy #EnergyIndependence #Russia #Rosatom