Search

ለኢትዮጵያ ክብር የቆመ ትውልድ!

ሰኞ መጋቢት 28, 2018 402

ኢትዮጵያ በዘመናት የፖለቲካ ውጣ ውረዶች፣ በውስጥ ሽኩቻዎች እና በውጭ ጂኦ-ፖለቲካዊ ተፅዕኖዎች ምክንያት ክብሯ ሲደፈር፣ ስሟ ከችጋር እና ከጥገኝነት ጋር ሲቆራኝ የኖረበት ዘመን ዛሬ ላይ ጥላው እየተገፈፈ አዲስ የብርሃን አድማስ ከእኛ አልፎ ወደ ውጭ እያንፀባረቀ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ክብር በሁሉም መስኮች እያንሰራራ፣ አንገቷን በኩራት ቀና የሚያደርግ አዲስ ዘመን እየተበሰረ ነው። ይህ ዘመን፣ ከምንም በላይ፣ "ለኢትዮጵያ ክብር የቆመ ትውልድ" መፈጠሩ በተግባር የተረጋገጠበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው። 

እውነተኛ ሉዓላዊነት እና የጥገኝነት ማብቂያ 

ሉዓላዊነት በድንበር መከለል እና በባንዲራ መውለብለብ ብቻ የሚረጋገጥ ፅንሰ-ሐሳብ አይደለም። እውነተኛ ሉዓላዊነት ከጥገኝነት አረንቋ ወጥቶ በራስ አቅም መቆምን፣ ብሔራዊ ጥቅምን በነፃነት ማስከበርን እና የዜጎችን ሁለንተናዊ ደኅንነት ማረጋገጥን ይጠይቃል። 

የዛሬው ትውልድ ይህንን የሉዓላዊነት ጥልቅ ምስጢር በሚገባ ተረድቶታል። ለዓመታት የተጫነብንን የልመና፣ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት እና የውጭ ስንዴ ጠባቂነት አስተሳሰብ ሰብሮ፣ ከጥገኝነት ወደ እውነተኛ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት የሚያደርገውን ጉዞ በጽናት ተያይዞታል።

የምግብ ሉዓላዊነት፦ የድል ማማ 

የዚህ ትውልድ አንፀባራቂ የክብር ማሳያ አንዱ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ያለው ታላቅ ሀገራዊ ተጋድሎ ነው። "የራሱን ጉርስ በራሱ ማምረት ያልቻለ፣ የዕለት ዳቦውን ከውጭ የሚለምን ሕዝብ እውነተኛ ፖለቲካዊ ነፃነት ሊኖረው አይችልም" የሚለውን የማይናወጥ እውነት በመገንዘብ፣ ኢትዮጵያውያን የከፈቱት አረንጓዴ አብዮት አስደናቂ ፍሬ እያፈራ ነው።

በስንዴ ልማት፣ በተለይም በበጋ መስኖ የተመዘገበው ታሪካዊ ድል፣ ኢትዮጵያ ከስንዴ ተመጽዋችነት ወደ ላኪነት ያደረገችው ዐቢይ ሽግግር የብሔራዊ ኩራታችን እና የክብራችን መገለጫ ነው። ከዚህም ባሻገር፣ "የአረንጓዴ አሻራ" የኅልውና ጉዟችን፣ ምድራችንን በማልበስ የተፈጥሮ ሉዓላዊነታችንን የምናስከብርበት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ እጃችንን እንደማንሰጥ ያረጋገጥንበት እርምጃ ሆኗል። 

ሁለንተናዊ ብሔራዊ አቅም

የሉዓላዊነት እና የክብር ጉዟችን በግብርናው ዘርፍ ብቻ የተገደበ አይደለም። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ የቁርጠኝነት ሐውልት፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችን ግዙፍ ማማ ነው። ምንም ዓይነት የውጭ ጫና፣ የዲፕሎማሲ ሽኩቻ እና ዛቻ ሳያበግረው፣ በራሱ ላብ እና ገንዘብ ግድቡን ከዳር ለማድረስ ሌት ተቀን የሚጋደለው ትውልድ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ጠባቂ መሆኑን በተግባር አስመስክሯል።

በቴክኖሎጂው ዘርፍ፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በዲፕሎማሲው መድረክ፣ እንዲሁም ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ እና ብቁ መከላከያ ሠራዊት በመገንባት ረገድ የተመዘገቡት ስኬቶች፣ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ብሔራዊ አቅም በጠንካራ አለት ላይ ያቆሙ የሉዓላዊነት ገድሎች ናቸው።

የታሪክ ስብራትን የመጠገን ራዕይ

ይህ ትውልድ አሁን ደግሞ ትኩረቱን ወደ አንዱ እና ዋነኛው የታሪክ ስብራት አዙሯል - እሱም የባሕር በር ጥያቄ ነው! ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት፣ የቀጣናው የኢኮኖሚ ሞተር እና የፖለቲካ ማዕከል የሆነችው ታላቋ ኢትዮጵያ፣ የባሕር በር ባለቤትነት መብቷ መረጋገጥ የፍትሕ፣ የሚዛናዊነት፣ እና የረጅም ጊዜ ሀገራዊ ኅልውና መሠረት ነው።

የምግብ ሉዓላዊነትን በተግባር እውን ያደረገው ይህ አረንጓዴ ትውልድ፣ ጫናዎችን ተቋቁሞ የሕዳሴውን ግድብ ያቆመው ይኸው የማይበገር ሕዝብ፣ የባሕር በር ጥያቄውንም መመለሱ አይቀሬ ታሪካዊ ሐቅ ነው። 

ለኢትዮጵያ ክብር የቆመ ትውልድ፣ ያነገበውን ብሔራዊ ራዕይ ዳር ሳያደርስ ወደኋላ አይመለስም! የኢትዮጵያ ክብር በልጆቿ እጅ ገናና ሆኖ ይቀጥላል! 

 

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ 

#Ethiopia #EBC #selfrelience #dignity #generation