Search

የቀይ ባሕር ደኅንነት እና የኢትዮጵያ የማይተካ ስትራቴጂካዊ ሚና

ረቡዕ መጋቢት 30, 2018 356

የቀይ ባሕር ሰማያዊ ሞገዶች ለዘመናት የአህጉራት መገናኛ፣ የታላላቅ ሥልጣኔዎች መናገሻ እና የዓለማችን የንግድ የደም-ስር ሆነው ቆይተዋል።

ይህ ባሕር ዛሬም ቢሆን የሸቀጦች መተላለፊያ ብቻ ሳይሆን፤ የታላላቅ ኃያላን ሀገራት የፖለቲካ ፍላጎት፣ የኢኮኖሚ የበላይነት ሽኩቻ እና የቅርቦቹም የሩቆቹም የሚፋለሙበት ግዙፍ የጂኦ-ፖለቲካዊ መድረክ ነው።

የአክሱም መንግሥት በዓለም ላይ ከነበሩ አራት ታላላቅ ኃያላን አንዱ ሊሆን የቻለው፣ በአዱሊስ እና በሌሎችም ወደቦች አማካኝነት የቀይ ባሕርን ንግድ እና ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ይቆጣጠር በነበረበት ወቅት ነው። ዛሬ ያ የፀጥታ አስተማማኝነት ፈተና ውስጥ ገብቶ ይታያል።

ይህም የሚያስተምረን አንድ እውነት አለ፦ ኢትዮጵያ ከባሕር ስትለይ ቀጠናው ለስጋት እና ለባዕዳን ጣልቃ ገብነት ይጋለጣል፤ ኢትዮጵያ ወደ ባሕር ስትጠጋ ግን የአካባቢው ሰላም እና ብልጽግና የታመነ መልህቅ ያገኛል።

በታኅሣሥ ወር 1943 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያስተላለፈው ውሳኔ 390፣ ኢትዮጵያ ለብሔራዊ ደኅንነቷ እና ለኢኮኖሚዋ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ፍላጎት "ሊገሰስ የማይችል" መሆኑን በማረጋገጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ የሕግ ማኅተም አሳርፎበታል።

ዛሬም ቢሆን የዓለም አቀፍ የባሕር ሕግ ኢትዮጵያን መሰል ሀገራት ወደ ባሕር የመድረስ እና የባሕር ውስጥ ሀብቶችን የመጠቀም ተፈጥሮአዊ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።

ዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞች እና የስትራቴጂ ጥናት ተቋማት እንደሚስማሙበት፣ የቀይ ባሕር ደኅንነት በባሕሩ ላይ በሚደረግ ጥበቃ ብቻ የሚረጋገጥ አይደለም።

የባሕር ላይ ወንበዴነት፣ ሽብርተኝነት እና ሕገ-ወጥ ዝውውር ምንጫቸው የየብስ ላይ አለመረጋጋት ነው። ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ ለዓመታት የሰላም አስከባሪ ኃይል በመሆን ያላትን ስም በቀይ ባሕር ላይ በመድገም፣ ቀጠናውን ከጥቃት የመከላከል ብርቱ አቅም አላት።

የኢኮኖሚው የደም-ስር እና የጸጥታው ጋሻ

የቀይ ባሕር አስፈላጊነት በቁጥሮች ሲገለጽ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል። በየዓመቱ ከዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ንግድ ውስጥ እስከ 12 በመቶ የሚሆነው በዚህ መስመር የሚያልፍ ሲሆን፣ በየቀኑ ከ9 ሚሊዮን በርሜል በላይ ነዳጅ ይጓጓዝበታል።

በቅርቡ በጥር ወር 2018 ዓ.ም በተመዘገቡ መረጃዎች መሠረት፣ በቀጠናው የተፈጠረው አለመረጋጋት መርከቦች አፍሪካን እንዲዞሩ በማድረጉ ምክንያት፣ በዓለም አቀፍ የሸቀጦች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ አስከትሏል።

ይህ ሁኔታ የሚያሳየው፣ የቀይ ባሕር ሰላም መደፍረስ የዓለምን ኢኮኖሚ እስከ 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ ሊያጋጥመው እንደሚችል ነው።

ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ የሕዝብ ቁጥርና ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር እንደመሆኗ፣ በቀይ ባሕር ላይ በቋሚነት መገኘቷ የውጭ ኃይሎችን ያልተመጣጠነ የበላይነት በማመጣጠን "የአካባቢው ሰላም በአካባቢው ሀገራት" የሚለውን መርህ ዕውን ለማድረግ ይረዳል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ የጀመረችው የባሕር ኃይል ግንባታ እና ያስመረቀቻቸው የዕዝ ማዕከላት፣ ለባሕሩ ደኅንነት ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያሳዩ ናቸው። ይህ ኃይል ለቀጠናው ሀገራት ስጋት ሳይሆን፣ የባሕር ላይ የንግድ መስመሮችን ከጥቃት ለመከላከል የሚቆም "የሰላም ጋሻ" ነው። 

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ በአካባቢው የሚታዩ ግጭቶች ወደ ኢኮኖሚ ትስስር እና የጋራ ብልጽግና እንዲቀየሩ ትልቅ የልማት ሞተር ይሆናል።

ያለ ኢትዮጵያ ተሳትፎ የሚመሰረት ማንኛውም የቀይ ባሕር የጸጥታ መዋቅር፣ ትልቅ የኃይል ክፍተት ያለባቸው እና ውጤታማነታቸው አጠራጣሪ መሆኑን ጂኦ-ፖለቲካዊ እውነታው ያስገድደናል።

"ባሕሩ ኢትዮጵያን ይፈልጋል!" የሚለው አባባል መሠረቱ የጂኦ-ፖለቲካ እውነታ ነው። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ ቋሚ፣ ሕጋዊ እና አስተማማኝ ቦታ ማግኘቷ ለዓለም አቀፍ ንግድ አስተማማኝ ጥበቃ የሚሰጥ ጠንካራ ኃይል ይፈጥራል፤ የውጭ ኃይሎችን ያልተገደበ ጣልቃ ገብነት በማመጣጠን የቀጠናውን ሉዓላዊነት ያጠናክራል።

ኢትዮጵያ ወደ ባሕር መጠጋቷ ለሀገራችን የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ሁሉ፣ ለቀይ ባሕርም ሚዛኑን የጠበቀ፣ በታላቅ ሀገር የሚመራ እና ዘላቂ ሰላም የሰፈነበት ቀጠና ለመሆን የኢትዮጵያ መገኘት ግድ ነው።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ለምሥራቅ አፍሪካ ብልጽግና አዲስ ንጋት፣ ለቀይ ባሕር ደኅንነት ደግሞ አስተማማኝ መልህቅ ነው!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት የትውልድ ጥያቄን በብቃት ትመልሳለች!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

#EBC #Ethiopia #RedSea