የኢትዮጵያ የኑክሌር ኃይል ኮሚሽን (ENEC) ከአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (ASTU) ጋር በአዲስ አበባ በሚገኘው የኮሚሽኑ ዋና መሥሪያ ቤት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ የኑክሌር ፖሊሲ እና በዓለም አቀፍ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) መስፈርቶች መሠረት በኑክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ሰላማዊ አጠቃቀም ዘርፍ የተቀናጀ እና ዘላቂ የትብብር ማዕቀፍ ለመፍጠር ያለመ ነው።

ትብብሩ በዋናነት በሰው ኃይል ልማት፣ በሥርዓተ ትምህርት ንድፍ እና አካዳሚክ ልማት፣ በምርምር እና ልማት፣ በተግባራዊ ሥልጠና፣ በአቅም ግንባታ እንዲሁም በሳይንሳዊ ዝግጅቶች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፤ የሁለቱ ተቋማት አመራሮች ስምምነቱ ለሀገራዊ ልማትና ዕድገት ፋይዳው የላቀ መሆኑን በመግለጽ ውጤታማ ስራዎችን ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የመግባቢያ ሰነዱን የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለሚ ጉታ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ የኑክሌር ኃይል ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሳንዶካን ደበበ መፈራረማቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።