Search

ፒኤስጂ ከአርሰናል ተጠባቂው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ

ቅዳሜ ግንቦት 22, 2018 40

በሃንጋሪ ቡዳፔስት ፑስካሽ አሬና ዛሬ ምሽት 1 ሰዓት ላይ የሚጀምረው የፒኤስጂ እና የአርሰናል የታላቁ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በመላው ዓለም በሚገኙ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ በከፍተኛ ጉጉት ይጠበቃል።

በታሪኩ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን አንስቶ የማያውቀው አርሰናል በዘንድሮው የውድድር ዘመን ይህን ታሪክ ለመቀየር ቆርጦ የተነሣ ይመስላል።

አርሰናል በውድድር ዓመቱ 22 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሣታቸው እና በሻምፒዮንስ ሊጉ ሳይሸነፉ ለፍጻሜ መድረሳቸው በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ትልቅ ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

የመድፈኞቹ የተከላካይ ክፍል በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ያስተናገደው ሁለት ግቦችን ብቻ ሲሆን፣ ይህም የአርቴታን ቡድን የማይበገር አድርጎታል።

የፓሪሱ ሀብታም ክለብ ለተከታታይ ሁለተኛ ዓመት ባለ ትልቅ ጆሮውን ዋንጫ ለማንሣት በቀሪ 90 ደቂቃዎች ይፋለማል።

በሉዊስ ኤንሪኬ የሚመሩት ፒኤስጂዎች አምና አርሰናልን በግማሽ ፍጻሜ በደርሶ መልስ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን፣ ዘንድሮም አርሰናልን አሸንፈው የአውሮፓ ንግሥናቸውን እንደሚያስቀጥሉ የቡድኑ አባላት ተናግረዋል።

አሠልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ዛሬ የፍፃሜ ጨዋታውን ማሸነፍ ከቻሉ እንደ ፔፕ ጋርዲዮላ፣ ቦብ ፔይስሊ እና ዚነዲን ዚዳን ሦስት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ያነሡ ጥቂት ስኬታማ አሠልጣኞች ተርታ በመሰለፍ ስማቸውን በታሪክ ማሕደር መጻፍ ይችላሉ።

በዛሬው ጨዋታ በፒኤስጂ በኩል አችራፍ ሐኪሚ፣ ኑኖ ሜንዴዝ እና ኡስማን ዴምቤሌ ጨዋታውን ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸውን አሠልጣኝ ሉዊስ ኤንሪኬ ተናግረዋል።

በአርሰናል በኩል ወሳኙ ተከላካይ ዩሪየን ቲምበር ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሠ ሲሆን ይህም ስብስቡን ይበልጥ ያጠናክረዋል ተብሏል።

ምሽት 1 ሰዓት በፑሽካሽ አሬና የሚጀምረው ጨዋታ አርሰናልን በትልቁ መድረክ ያነግሣል? ወይስ የፓሪሱን ቱጃር ክለብ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ያደርጋል? የሚለው ጥያቄ መልስ ያገኛል።

እርስዎስ በአውሮፓ መድረክ ታላቅ የሆነውን ዋንጫ ማን ያነሣል ብለው ያስባሉ?

በዘረንቶስ ሰለሞን