ያለ አስተማማኝ አህጉራዊና ቀጠናዊ ሰላም ልማትና ዕድገትን ማረጋገጥ እንደማይቻል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።
ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ ካሁን ቀደም የተፈራረሙትን የሁለትዮሽ ወታደራዊ ትብብርን ስምምነት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማድረስ ያለመ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በዕለቱ በሞዛምቢክ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በጄኔራል ጁሊዮ ዶ ስሳንቶስ ጃኔ የተመራ ልዑክ በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ መምሪያ ሲደርስ በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

የአትዮጵያ እና የሞዛምቢክ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች በተገኙበት የውይይት መድረክ ላይ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አውስተው በሀገራቱ መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት በ"ፓን-አፍሪካኒዝም" መርሆዎች፣ አንድነት፣እና ጽናት፣ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ምዕራፍ መሸጋገር መቻሉን የገለጹት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው በወዳጅነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት መጠናከር የቀጠናውን ሠላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል።
ያለ ሠላምና ፀጥታ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግናን ማሳካት እንደማይቻል የተናገሩት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ሽብርተኝነትን በጋራ በመዋጋት፣ በሳይበር ደኅንነትና መሠል የትብብር መስኮች ዙሪያ በቅንጅት በመስራት አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ሠላምን ለማረጋገጥ ፣ ሀገራቱ በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የሞዛምቢክ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄኔራል ጁሊዮ ዶ ስሳንቶስ ጃኔ በበኩላቸው ሁለቱ ሀገራት በልዩ ልዩ የወታደራዊ ትብብር መስኮች ዙርያ በትብብር መስራታቸው ለአህጉራዊ እና ቀጠናዊ ሰላም መረጋገጥ የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጄኔራል ጁሊዮ ዶ ሳንቶስ ጃኔ አክለውም ከአትዮጵያ ጋር በዘርፈ ብዙ ወታራዊ የትብብር መስኮች ዙርያ በቅንጅት መስራታችን በትምህርት እና ስልጠና ሰፊ ልምድ እና ተሞክሮ ለማግኘት ያስችልናል ብለዋል፡፡

የመከላከያ ውጪ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ የተካሄደው የሁለትዮሽ መድረክ ሀገራቱ ከአሁን ቀደም የተፈራረሙትን ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ወደ ተግባር የቀየረ እና ቀጣይ በሚሰሩ የትብብር ማዕቀፎች ዙሪያ አቅጣጫ ያስቀመጠ ውይይት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለቀጠናው ሰላም እና ልማት መረጋገጥ ካላት ቁርጠኝነት የተነሳ ሞዛንቢክን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በተለያዩ ወታደራዊ ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እያሳዩ እንደሚገኙ የገለጹት ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ መከላከያ እንደተቋም ያካሄደው የሪፎርም ስራ ውጤት በመሆኑ የተካሄደው የሁለትዮሽ መድረክ እንደ ሀገርም ሆነ እንደተቋም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡