የፊታችን ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሀገራችን የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነጻ፣ ገለልተኛና ተአማኒነት ያለው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት እንዲሰፍን ለማድረግ የምርጫ ታዛቢዎች ሚና በግንባር ቀደምትነት እንደሚጠቀስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
በዚህ ታሪካዊና ሀገራዊ የዴሞክራሲ ጉዞ ላይ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የውጭ ታዛቢዎች እና የዕጩ ወኪሎች በታዛቢነት በይፋ የሚሳተፉ ሲሆን ሁሉም ተሳታፊዎች ከምርጫ ቦርድ ሕጋዊ የምስክር ወረቀት የወሰዱ መሆናቸው ተረጋግጧል።
በተለይም ምርጫውን በገለልተኝነት ለመታዘብ ኃላፊነት የወሰዱት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከማንኛውም ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የጸዱ፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙና ከመንግሥት ተጽዕኖ ነጻ መሆን እንደሚገባቸው በሕግ ተደንግጓል።

የዚህን 7ኛ ጠቅላላ ምርጫ ፍጹም ተአማኒነትና ግልጽነት ለማረጋገጥ በርካታ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ተቋማት ታዛቢዎቻቸውን በስፋት ያሰማሩ ሲሆን በዚህም መሠረት 55 የሀገር ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ታዛቢዎች፣ 59 አባላትን ያቀፈው የአፍሪካ ኅብረት (AU) የታዛቢ ቡድን እንዲሁም 26 አባላት ያሉት የኢጋድ (IGAD) የታዛቢ ቡድን በሂደቱ ላይ በይፋ ስምሪት አግኝተው በሥራ ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ ታዛቢዎች በየምርጫ ጣቢያዎቹ በአካል ተገኝተው ሂደቱን በነጻነትና በቅርበት የመከታተል፣ ከሚመለከታቸው የምርጫ አስፈጻሚዎች መረጃ ጠይቆ የማግኘት፣ የድምፅ አሰጣጥና የቆጠራ ሂደቱን በቀጥታ የመታዘብ እንዲሁም በታዛቢነት ወቅት ያስተዋሏቸውን ማናቸውንም ጉድለቶች በቀጥታ ለቦርዱ የማቅረብ መብት ተሰጥቷቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች በምርጫ ክልልና በጣቢያ ደረጃ ሂደቱን የሚከታተሉላቸውን ተቀማጭና ተዘዋዋሪ ወኪሎችን የመመደብ ሙሉ መብት እንዳላቸው ታውቋል።
ይሁን እንጂ የዴሞክራሲ ሂደቱ ሰላማዊ፣ ስልጡንና ሥርዓትን የጠበቀ ይሆን ዘንድ ታዛቢዎች የተጣለባቸውን ሕጋዊ ግዴታዎች በአግባቡ የመወጣት ኃላፊነት አለባቸው። በመሆኑም የታዛቢነት መታወቂያቸውን በማንኛውም ጊዜ ይዞ መገኘት፣ የምርጫ አስፈጻሚዎችን መመሪያና ሕጋዊ አሠራር ማክበር፣ ከማንኛውም የምርጫ መስተጓጎልና ጣልቃ-ገብነት መቆጠብ እንዲሁም የታዘቧቸውን ዝርዝር ሪፖርቶች ለምርጫ ቦርዱ ማቅረብ ከታዛቢዎቹ የሚጠበቁ ግዴታዎች ናቸው።
የምርጫውን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ የተቀመጠው ሕጋዊ መስመር ጥብቅ በመሆኑ ታዛቢዎች ከተሰጣቸው የሥነ-ምግባር ደንብ ውጭ ሆነው ከተገኙ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ ጥፋቱ ክብደትና ሁኔታ ማስጠንቀቂያ ከመስጠት ጀምሮ ከታዛቢነት እስከ ማገድ የሚደርስ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ተጠቅሷል።
በአጠቃላይ የታዛቢዎች ሚና በሙሉ ገለልተኝነትና በሕግ አክባሪነት ማዕቀፍ ላይ መመሥረቱ ለምርጫው ስኬታማነት ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እጅግ ወሳኝ መሠረት እንደሆነ ይታመናል።
በበረከት ሽመልስ