ከ80 ዓመታት በፊት በአንድ ወታደራዊ አውሮፕላን ሥራውን የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ዛሬ የአህጉሪቱ ቁንጮና የኢትዮጵያውያን ኩራት ሆኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ እንደገለጹት፤ የዚህ ተቋም ስኬት ለሀገራዊ ብልጽግና ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ሲሆን፣ ስኬቱም በአራት ዋና ዋና ምሶሶዎች ላይ የቆመ ነው።

የአየር መንገዱ ዋነኛ የስኬት ምስጢር ራሱን የቻለ የኮርፖሬት ባህል መገንባቱ ነው።
ተቋሙ ከመንግሥትም ሆነ ከሌሎች ወገኖች ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ፣ በቢዝነስ ሕግና በባለሙያ አመራር ብቻ መመራቱ ለዛሬው ውጤት አብቅቶታል።
ይህም ለሁሉም በእኩል የሚያገለግልና የሁሉንም ጥቅም የሚያስከብር ሀገራዊ ተቋም እንዲሆን አድርጎታል።

በአየር መንገድ ዘርፍ "ደኅንነት" (Safety)፣ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት 80 ዓመታት ከዓለም ግዙፍ አየር መንገዶች ጋር ሲነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ የሚባል አደጋ ያጋጠመውና፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ አስተማማኝ ተብሎ የተመሰከረለት መሆኑ ለተጓዦች ተመራጭ እንዲሆን አድርጎታል።

የአየር መንገዱ አመራሮች በ8 ሰዓት የሥራ ገደብ የማይወሰኑ፣ በትጋትና በፈጠራ የታጀቡ ናቸው።
በሌላ በኩል 30 ሺህ የሚጠጉ ሠራተኞቹ ራሳቸውን እንደ "ሀገር ጠባቂ ወታደር" የሚቆጥሩ፣ ሌላው ሲተኛ የማይተኙና የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ ከፍ ለማድረግ የሚተጉ መሆናቸው የተቋሙ ትልቅ ሞተር ነው።

አየር መንገዱ ዘላቂ ተማሪ ነው። አዳዲስ አውሮፕላኖችና ቴክኖሎጂዎች በዓለም ላይ ሲፈጠሩ ለአፍሪካ በማስተዋወቅ ረገድ ሁሌም ቀዳሚ ነው።
ከበረራ አገልግሎት ባለፈ በጥገና፣ በትምህርትና አሁን ደግሞ የአውሮፕላን መለዋወጫዎችን እስከ ማምረት የደረሰ የዕውቀት ሽግግር ማድረጉ ለስኬቱ ቀጣይነት ዋስትና ሆኖታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬት በአጋጣሚ የመጣ ሳይሆን በጠንካራ አመራር፣ በሠራተኞች ዲስፕሊንና ዘመኑን በዋጀ የቢዝነስ ስልት የተገነባ ነው። ይህንን የ"ስኬት ቀመር" ወደ ሌሎች ሀገራዊ ተቋማት ማጋባት ከተቻለ፣ የሀገራችን የብልጽግና ጉዞ እውን መሆኑ የማይቀር ነው።
በላሉ ኢታላ