የብሪክስ (BRICS) ሀገራት ጥምረት በዓለም አቀፍ የንግድ መድረክ ላይ ያለውን አቋም በከፍተኛ ደረጃ እያጠናከረ ይገኛል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2025 የጥምረቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ መጠን ከ1 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ተሻግሯል።
ይህ ስኬት ጥምረቱን ከኢኮኖሚ ዕድገት ተስፋነት ባለፈ፣ ዓለም አቀፍ የሸቀጦች ፍሰትን ወደሚወስን ቁልፍ የንግድ ኃይልነት ቀይሮታል።
ብሔራዊ ገንዘቦች እና የኢኮኖሚ ጥንካሬ
የብሪክስ ሀገራት የንግድ ልውውጥ እያደገ የመጣው አባል ሀገራቱ በመካከላቸው በሚያደርጉት የንግድ እንቅስቃሴ የራሳቸውን ብሔራዊ ገንዘቦች መጠቀም በመጀመራቸው እንደሆነ የዘርፍ ተንታኞች ይገልጻሉ።
በአሁኑ ወቅት ከ67 በመቶ በላይ የሚሆነው የብሪክስ የንግድ ልውውጥ የሚከናወነው በአባል ሀገራቱ ገንዘቦች ነው። በተጨማሪም የብሪክስ ፕላስ (BRICS+) ሀገራት በዓለም አቀፍ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (Global GDP) ላይ ያላቸው ድርሻ 39.7 በመቶ በ2025 ደርሷል። ባለፉት አምስት ዓመታት ብቻ በአባል ሀገራቱ መካከል ያለው ንግድ በአማካይ በዓመት በ4.75 በመቶ ዕድገት አሳይቷል።
ቻይና እና ሕንድ፡ የንግድ ሞተሮቹ
ቻይና በብሪክስ ውስጥ የፍላጎት ማዕከል (Demand Anchor) በመሆን የምግብ፣ የኃይል እና ጥሬ ዕቃዎችን ከሌሎች አባላት በከፍተኛ ሁኔታ የምትገዛ ሲሆን፣ በምላሹም ዘመናዊ መሣሪያዎችንና የኢንዱስትሪ ምርቶችን የምታቀርብ የገበያ መሪ ሆናለች።
ከቻይና በተጨማሪ ሕንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ በትላልቅ የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ በመድኃኒት (Pharmaceuticals) እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላት ድርሻ ለጥምረቱ የንግድ ዕድገት ትልቅ ግብዓት ሆኗል። ሩሲያ እና ብራዚል በበኩላቸው በኃይል አቅርቦት እና በግብርና ምርቶች የጥምረቱን ፍላጎት በመሸፈን ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳዲስ አባል ሀገራት መቀላቀላቸውም የቡድኑን ሥነ-ሕዝባዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም ይበልጥ አጠናክሮታል።
የተፈጥሮ ሀብት እና የኢንዱስትሪ ትስስር
የብሪክስ ሀገራት በዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ሀብት ገበያ ላይ ያላቸው የበላይነት ጉልህ ነው። ጥምረቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚመረተው ድፍድፍ ዘይት 40 በመቶውን እንዲሁም ከዓለም የብረት ማዕድን ክምችት 30 በመቶውን ይቆጣጠራል።
ሩሲያ ከኃይል አቅርቦት ባለፈ በኬሚካል፣ በብረታ ብረት እና በምግብ ምርቶች የንግድ አድማሷን እያሰፋች ሲሆን፣ ብራዚል ደግሞ 36 በመቶ የሚሆነውን የጥምረቱን የግብርና ምርት ፍላጎት ትሸፍናለች። በተለይም ብራዚል ከሩሲያ በከፍተኛ መጠን የምታስመጣው ማዳበሪያ ለግብርና ዕድገቷ ዋነኛ መሠረት ሆኗል።
ሎጂስቲክስና ዲጂታል ቴክኖሎጂ፡ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎች
የብሪክስ ሀገራት በቆዳ ስፋትና በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የተራራቁ መሆናቸው ለንግድ እንቅስቃሴው የሎጂስቲክስ ወጪን ቢጨምርም፣ ይህንን ለመቅረፍ አዳዲስ የትራንስፖርት ኮሪደሮች በመገንባት ላይ ናቸው። ከእነዚህም መካከል፦
ሰሜናዊ የባህር መስመር (Northern Sea Route)፦ በአውሮፓ እና እስያ መካከል ያለውን ርቀት የሚያሳጥር።
የሰሜን-ደቡብ ኮሪደር (North-South Corridor)፦ ሩሲያን ከኢራን፣ ሕንድ እና ከባሕረ ሰላጤው ሀገራት ጋር የሚያገናኝ።
የፓን-አፍሪካ ትስስር፦ ከሩሲያ ሙርማንስክ እስከ ደቡብ አፍሪካ የሚዘልቅ የንግድ መስመር ሐሳቦች ተጠቃሽ ናቸው።
የጉምሩክ አሠራርን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማዘመንና ማቀናጀት ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ነው። ምንም እንኳን ሀገራቱ የራሳቸው የተለየ የንግድ ሕግና ደንብ ቢኖራቸውም፣ በካዛን በተደረገው ጉባኤ የአሠራር ሥርዓቶችን ለማቅለልና የንግድ እንቅፋቶችን ለማስወገድ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የወደፊት ተስፋዎች
የብሪክስ የንግድ ትስስርን ይበልጥ ለማሳለጥ "ብሪክስ ብሪጅ" (BRICS Bridge) የተሰኘ የክፍያ ሥርዓት እና የዲጂታል ገንዘቦችን (Digital Currencies) የመጠቀም ዝግጅት እየተደረገ ነው። በተጨማሪም እንደ "የብሪክስ የእህል ልውውጥ ማዕከል" (BRICS Grain Exchange) ያሉ ተቋማት መመሥረታቸው፣ አባል ሀገራቱ በምግብ ዋስትና እና በዋጋ ቁጥጥር ላይ የተሻለ አቅም እንዲኖራቸው ያደርጋል።
ስለሆነም፣ የብሪክስ ሀገራት በመካከላቸው ያለውን የንግድ ልውውጥ ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር፣ በምዕራባውያን ላይ ብቻ ተመሥርቶ የነበረውን የዓለም የንግድ ሥርዓት ወደ ሁለገብና ፍትሐዊ የንግድ ትስስር እየቀየሩት እንደሚገኙ የዘርፉ ምሁራን ይስማማሉ።
በሰለሞን ገዳ