Search

የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ - የታዳሽ ኃይል ልዕልና!

ሓሙስ ሚያዝያ 08, 2018 157

በኢትዮጵያ ተራራማ ሥፍራዎች እና ሰፋፊ ሜዳዎች ላይ ዛሬ አዲስ የለውጥ ንፋስ እየነፈሰ ነው።

ይህ ንፋስ ዝም ብሎ የሚያልፍ ሳይሆን፣ የሀገራችንን የኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያንቀሳቅስ፣ የጨለማ መንደሮችን የሚያበራ እና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ትንሣኤ የሚያበስር ታላቅ ኃይል ሆኗል።

ዛሬ በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ሄጦሳ ወረዳ፣ ኢተያ ላይ በደማቅ ሁኔታ የተመረቀው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ልማት የጀመረችውን ጉዞ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ሌላኛው ታሪካዊ አሻራ ነው።

የአሰላው ድል - የቴክኖሎጂ እና የጽናት ውጤት

ከአዲስ አበባ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ፣ በኢትዮጵያ የኢነርጂ ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ የሚሰጠው ፕሮጀክት ነው። በታኅሣሥ 2014 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ይህ ጣቢያ፣ በ145 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ የተከናወነ ነው።

ፕሮጀክቱ በዘመናዊነቱ እና በቴክኖሎጂ አቅሙ እስከ ዛሬ ከተገነቡት የንፋስ እርሻዎች የተሻለ ጥራት እና ብቃት ይዞ ብቅ ብሏል።

ጣቢያው በጠቅላላው 100 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያላቸው 29 ግዙፍ ተርባይኖችን የታጠቀ ነው። እያንዳንዱ ተርባይን 3.465 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፣ የ84 ሜትር ቁመት እና የ132 ሜትር የክንፍ ዲያሜትር ያላቸው እነዚህ "ነጭ ግዙፎች" በኢተያ ሰማይ ስር በኩራት መቆማቸው ለሀገር ተስፋ የሚሰጥ እይታ ነው።

በአካባቢው ያለው አማካይ የንፋስ ፍጥነት በሰከንድ 8.2 ሜትር መሆኑ፣ ጣቢያው በዓመት እስከ 354 ጊጋ ዋት በሰዓት ኃይል እንዲያመነጭ ያስችለዋል። ይህ ማለት በሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ ብርሃን እና ኃይል ያገኛሉ ማለት ነው።

ታዳሽ ኃይል - የኢትዮጵያ ብልህ ስትራቴጂ

ኢትዮጵያ በውኃ ሀብቷ "የምሥራቅ አፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማማ" መሆኗ ቢታወቅም፣ የኃይል ምንጯን በውኃ ላይ ብቻ (ከ90 በመቶ በላይ) ጥገኛ ማድረጓ ግን ስጋት ነበረው።

የአየር ንብረት መለዋወጥ እና ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት የውኃ መጠን ስለሚቀንስ የኃይል መቆራረጥ ይፈጠር ነበር። እዚህ ላይ ነው የንፋስ ኃይል "ተዓምራዊ" ሚና የሚጫወተው።

በተፈጥሮ ሚዛን በበጋ ወቅት የውኃ ግድቦች መጠን ሲቀንስ፣ የንፋስ ፍጥነት ደግሞ ይጨምራል። ይህ "ትክክለኛ ተዛማጅነት" (Complementarity) የኢትዮጵያን የኃይል ቋት በማረጋጋት ረገድ የጀርባ አጥንት ሆኗል።

ከአሰላ በፊት የተገነቡት አዳማ 1 እና 2 (204 ሜጋ ዋት)፣ አሸጎዳ (120 ሜጋ ዋት) እና አይሻ 2 (80 ሜጋ ዋት) በአሁኑ ወቅት ከ500 ሜጋ ዋት በላይ የንፋስ ኃይል ለብሔራዊ ቋት እያበረከቱ ይገኛሉ።

ነገር ግን ይህ ገና ጅምር ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ እስከ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት የንፋስ ኃይል የማመንጨት ዕምቅ አቅም አላት። ይህን ሀብት ወደ ተግባር ለመቀየር መንግሥት የወሰደው የፖሊሲ ማሻሻያ እና የግሉን ዘርፍ የመንግሥት እና የግል አጋርነት (PPP) ማዕቀፍ እንዲሳተፍ ማድረጉ፣ የኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይል ተዓምር ይበልጥ ያፋጥነዋል።

በቅርቡ የሚጀመሩት አይሻ 1 እና 3 ፕሮጀክቶች ከ300 ሜጋ ዋት በላይ ኃይል በግል ባለሀብቶች እንዲመነጩ መታቀዱ ለዚህ ማሳያ ነው።

ዓለም አቀፋዊ ዳራ እና የኢትዮጵያ ቦታ

የንፋስ ኃይል ልማት ታሪክ እ.ኤ.አ በ1883 በቪየና ከታየው የመጀመሪያ ተርባይን ጀምሮ ብዙ ርቀት ተጉዟል። በ1973 የተከሰተው የዓለም የነዳጅ ቀውስ ሀገራት ወደ አማራጭ ኃይል እንዲዞሩ ግፊት አድርጓል።

ዛሬ ቻይና በጁኳን የንፋስ እርሻ እስከ 7 ሺህ 965 ሜጋ ዋት በማመንጨት ዓለምን እየመራች ሲሆን፣ ሕንድና አሜሪካም ተከታዩን ደረጃ ይዘዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ዓለም አቀፍ ፉክክር ውስጥ የአፍሪካ ፋና ወጊ ሆና ብቅ ብላለች። የንፋስ ኃይል ማመንጫ ግንባታ የቴክኖሎጂ ሽግግርንም ይዞ ይመጣል።

የአሰላ ፕሮጀክት ሲገነባ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች እና ባለሙያዎች የንፋስ ተርባይን ተከላ እና ጥገና ዕውቀትን ቀስመዋል። ይህ የዕውቀት ሽግግር ለሀገራችን የነገ ጉዞ ትልቅ ካፒታል ነው።

ከብርሃን ባሻገር - ኢኮኖሚያዊ እና ቀጣናዊ ፋይዳዎች

የንፋስ ኃይል ልማት ለኢትዮጵያ ከብርሃን ባለፈ በርካታ ፋይዳዎች አሉት። አንደኛው እና ዋነኛው የኢንዱስትሪ መፋጠን ነው። ያለ አስተማማኝ ኃይል ፋብሪካዎች ሊንቀሳቀሱ አይችሉም። የንፋስ ኃይል ጣቢያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች አቅራቢያ መገንባታቸው የምርት ዕድገትን በማረጋገጥ የገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት (Import Substitution) ትልቅ እገዛ ያደርጋል።

ሁለተኛው ጉዳይ ቀጣናዊ ትሥሥር ነው። ኢትዮጵያ "የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ማዕከል" (Energy Hub) የመሆን ራዕይ አላት። ዛሬ ለጅቡቲ፣ ለሱዳን እና ለኬንያ ኤሌክትሪክ በመላክ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የውጭ ምንዛሬ እያገኘች ነው። የታዳሽ ኃይል ምንጮቻችን ሲሰፉ፣ ይህ ገቢ እጥፍ ድርብ ሆኖ የሀገራችንን የውጭ ምንዛሬ እጥረት በዘላቂነት ይፈታዋል።

ሦስተኛው እና ወሳኙ ነጥብ አረንጓዴ አሻራ ነው። ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በከፍተኛ ስጋት ውስጥ በወደቀችበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ዜሮ የካርቦን ልቀት ያለውን የታዳሽ ኃይል አማራጭ መከተሏ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደርገዋል።

ይህ አቅጣጫ ከታላቁ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ጋር ተዳምሮ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት በተግባር ያሳያል።

የተስፋው ጎህ

የአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ምርቃት ተራ የግንባታ ፍጻሜ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ብሩህ መፃኢ ዕድል ማሳያ ነው። ሀገራችን ተፈጥሮ ያደላላትን የንፋስ፣ የውኃ፣ የፀሐይ እና የእንፋሎት (Geothermal) ሀብቶች በአግባቡ በማልማት የአፍሪካ የንጹህ ኃይል ፋና ወጊ መሆኗን አረጋግጣለች።

ዛሬ በአሰላ ምድር የሚሽከረከሩት 29 ተርባይኖች፣ የኢትዮጵያ የብልፅግና ተሽከርካሪዎች ናቸው። እነርሱ ሲሽከረከሩ ፋብሪካዎች ያመርታሉ፣ ተማሪዎች በብርሃን ያጠናሉ፣ ሆስፒታሎች ሕይወት ያተርፋሉ፣ ኢኮኖሚውም ከፍ ይላል።

የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ተዓምር ገና ጅማሮ ላይ ቢሆንም፣ አሁን የታየው ጽናት እና ስኬት ግን ሀገራችን በቅርቡ የዓለም የታዳሽ ኃይል ተምሳሌት እንደምትሆን ጥርጥር የለውም። ነፋሳችን ኃይል ሆኗል፤ ኃይላችን ደግሞ ወደ ብልፅግና የሚወስደን ብሩህ ብርሃን ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

#EBC #Ethiopia #renewableenergy #greenmobility