ሀገራዊ ምክክር ከአድማስ ባሻገር የሚናፈቅ የሩቅ ህልም ሳይሆን ካለፈው ዘመን የትርክት ስንጥቆች ተሻግረን ነገን በፅኑ መሰረት ላይ የምንገነባበት የሰለጠነ የሃሳብ ድልድይ ነው።
በሀገር ታሪክ ውስጥ እንደ ማዕበል የሚነሱና የሚወርዱ የሃሳብ ወጀቦችን አቅጣጫ የሚያስይዝ የነገዋን ሀገር መልክና ቁመና የሚወስን እጅግ ወሳኝ ተግባር ቢኖር ምክክር ነዉ፡፡ ይህም ልዩነቶችን ለቅሞ አውጥቶ፣ በአጀንዳነት ቀርጾ መድረክ ላይ ማሰጣት ነው።
ይህ የምክክር አጀንዳ የመቅረጽ ሂደት በራሱ ቀላል ና መደበኛ ስራ ሳይሆን የኢትዮጵያን ዘርፈ-ብዙ ህመም የሚያዳምጡበትና ፈውስ የሚፈልጉበት ታላቅ የፖለቲካ ጥበብ ነው።
በአለምአቀፍ የታሪክ መዝገብ ላይ እንደምናየው አንዳንድ ሀገራት አጀንዳዎቻቸውን ከላይ ከጥቂት የፖለቲካ መሪዎችና ሊሂቃን ማዕድ ብቻ ቆርሰው ሂደቱን ይጀምሩታል። ያ አካሄድ መንገዱን ቢያሳጥርም ህዝብን ባይተዋር የሚያደርግና ለጥቂቶች ብቻ የተበጀ ጠባብ በር ነው።
በሌላ በኩል አጀንዳዎችን መቅረጽ ራሱ ታላቅ ህዝባዊ ንቅናቄ ሆኖ ከሁሉም ማህበረሰብ ጓዳና ደጅ የሚሰበሰብበት አማራጭ አለ። ይህኛው መንገድ ሀብትና ጊዜ የሚጠይቅ፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ቢሆንም፣ እያንዳንዱ ዜጋ የሂደቱ ባለቤትና የውሳኔው ባለድርሻ እንዲሆን ያደርጋል።
በኢትዮጵያችን አሁን እየተመራ ያለው ሀገራዊ ምክክርም አጀንዳዎቹ አስቀድመው በህግ የታጠሩና የተወሰኑ ባለመሆናቸው፣ በራሱ ትልቅ የዲሞክራሲ ማሳያ ነው።
በሀገራችን ያሉ የሃሳብ ልዩነቶችና የትርክት ስንጥቆች እጅግ መሰረታዊ በመሆናቸው፣ ምናልባትም አጀንዳዎቹ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ አስቀድመው ተደንግገው ቢሆን ኖሮ ያ በተገደበ ኃይል የተወለደ አጀንዳ በርካታ ተቃውሞዎችን መውለዱና ገና ሳይጀመር መቀጨቱ የማይቀሬ ነበር።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህንን ስጋት በመስበር በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት ይዞ ወደ ህዝብ ወርዷል።
አጀንዳዎችን ከተሳታፊዎች፣ ከቡድኖች፣ ከጥናቶች፣ ከግለሰቦችና ከተለያዩ ተቋማት በማሰባሰብ ታላቅ የታሪክ ስራ አከናውኗል። እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት እውነታ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡት ጉዳዮች የህዝቡ የልብ ትርታና የሃሳብ ግብዓቶች ሲሆኑ እነዚያን ግብዓቶች አበጥሮ፣ ፈርጅ አስይዞና ቀርጾ ይፋ የማድረግ ብቸኛ ስልጣን ያለው የኮሚሽኑ ምክር ቤት ነው።
ኮሚሽኑ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ 93 በመቶ የሚሆኑትን የሀገራችን ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ተደራሽ ማድረግ መቻሉ፣ ይህ ጉዞ ከገጠር እስከ ከተማ፣ ከገበሬው እስከ ምሁሩ ድረስ የደረሰ እውነተኛ ህዝባዊ መሰረትና የጸና ተአማኒነት እንዳለው ትልቅ ማረጋገጫ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ ማህበረሰቦችና የፖለቲካ ሃይሎች የተሰበሰቡት ግብዓቶች በጥንቃቄ ተለይተው ወደ አጀንዳነት ተቀይረዋል። ከተሰበሰቡት የሃሳብ ክምችቶች መካከል እጅግ መሰረታዊና ሀገራዊ የሆኑትን የልዩነት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱትን እንዲሁም ጥልቀትና አግባብነታቸውን በመመዘን የማጠናከርና የመቅረጽ ሂደቱ ተከናዉኗል።
እነዚህ አጀንዳዎች ተለይተውና ቅደም ተከተል ተሰጥቷቸው ለህዝብና ለባለድርሻ አካላት ይፋ መደረጋቸው ደግሞ ለምክክር መድረኩ ወሳኝ ነው።
አጀንዳዎችን ይፋ ማድረግና ሂደቱን ማካሄድ ግልጽነትና ተአማኒነት በማስፈን ጥርጣሬን ያጠፋል። እንዲሁም ተሳታፊዎች በሚወያዩባቸው ነጥቦች ላይ በቂ ዝግጅትና ጥናት አድርገው እንዲቀርቡ ስለሚረዳ፣ ውይይቱ በስሜትና በጩኸት ሳይሆን በዕውቀትና በምክንያት ላይ የተመሰረተ የሰለጠነ መድረክ እንዲሆን ያደርጋል።
ከሁሉም በላይ ግን ለዘመናት የኖርንባቸውን ውስብስብ የፖለቲካና የማህበራዊ አለመግባባቶች ስር-ነቀል መንስኤዎች አውጥተን እንድንጋፈጣቸው መንገድ ይከፍታል። የጠመንጃ ድምጽንና ግጭትን በማስቀረት፣ ልዩነቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት አዲስና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል በሀገራችን ውስጥ ይተክላል።
ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተገኘ እጅግ ውድና ብርቅዬ አጋጣሚ ፍሬያማ እንዲሆን የሀገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎችና እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል በቅን ልቦናና በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንዲቆሙ የወቅቱ ታሪካዊ ጥሪ ያስገድዳል።
ምክክሩ ሀገራችን ከገጠሟት ውስብስብ ፈተናዎች በሰላማዊ መንገድ እንድትወጣ ከማስቻሉም በላይ ቀጣዩ ትውልድ የሚረከባት፣ በሃሳብ የበለጸገችና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ዋነኛው የጽኑ መሰረት ድንጋይ ነው።
በበረከት ሽመልስ