ከ41 ዓመታት በፊት በቻይና ማኦዉሱ በረሃ ተንቀሳቃሽ አሸዋ መኖሪያ ቤቷን በግማሽ እስኪቀብር ድረስ ሕይወት አስቸጋሪ ሆኖባት የነበረ ቢሆንም፣ ይን ዩዠን የተባለችው ጀግና እናት ግን ለተፈጥሮ አስከፊ ፈተና እጅ አልሰጠችም።
በየቀኑ ማለዳ እየተነሳች አስከፊውን የሙቀት ወበቅ፣ ድርቅና የአሸዋ አውሎ ነፋስ በመቋቋም ባደረገችው የማይታክት ተጋድሎ፣ 28 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ በረሃማ መሬትን ወደ ለምለም በመቀየር በአንድ ወቅት ደረቅ በነበረው ምድር ላይ አዲስ ሕይወት ዘርታለች።
ለዚህ አስደናቂ ስኬቷ በወቅቱ በቻይና የእንግሊዘኛ መምህር ከነበረ አሜሪካዊ ጓደኛዋ ያገኘችው የ5 ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አስቸጋሪውን አካባቢ የሚቋቋሙ ችግኞችን እንድትገዛ ረድቷታል።
ዛሬ ላይ ያ ልገሳ አድጎ በአንድ ወቅት ምድረ በዳ በነበረው መሬት ላይ ከ50 ሺህ በላይ ዛፎች እንዲተከሉና አካባቢው ወደለመለመ ደን እንዲቀየር አድርጓል።
በቻይና የተፈጥሮ አደጋን በመጋፈጥ እንደ ይን ያሉ በርካታ ሰዎች ያሉ ሲሆን፣ ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሰፊ ሥነ-ምህዳራዊ መፍትሔዎችን በብሔራዊ ደረጃ በመተግበር ላይ ትገኛለች።
እ.ኤ.አ. በ1978 ታላቁ ሥነ-ምህዳራዊ ተልእኮ ከተጀመረ ወዲህ ባለፉት 48 ዓመታት ውስጥ ቻይና 32 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ ደን ጠብቃ ማቆየት የቻለች ሲሆን፣ 85.3 ሚሊዮን ሄክታር የተራቆተ የግጦሽ መሬት እንዲያገግምና የ44.6 ሚሊዮን ሄክታር የአፈር መሸርሸርን መቆጣጠር አስችሏል።
እነዚህ አስደናቂ ውጤቶች የተመዘገቡት የቴክኖሎጂ አቅምን ከተፈጥሮ ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር ሲሆን፣ በደረቃማ ክልሎች የተተከሉ የሶላር ፓነሎች የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባለፈ ጥላ በመጣል የውሃ ትነትን በመቀነስ የሰብል ዕድገትን ይደግፋሉ። ከዚህ ቀደም "የሞት ባሕር" የተባለው የኩቡቺ በረሃ ዛሬ ላይ ወደ ግዙፍ የሶላር እርሻነት ተቀይሯል።
ቻይና በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት አረንጓዴ እየሆነች ያለች ሀገር መሆንዋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (UNCCD) ዘንድ እውቅና ያገኘ ሲሆን፣ የበረሃማነት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዋንና ልምዷን እንደ ሞሪታኒያ እና ናይጄሪያ ላሉ የአፍሪካ ሀገራት ጭምር በማጋራት ላይ ትገኛለች።
እስከ 2030 ድረስም 12.4 ሚሊዮን ሄክታር የተራቆተ መሬትን ለማከም እና የአረንጓዴ በረሃ ኢንዱስትሪን ይበልጥ ለማስፋፋት አቅዳ እየሰራች ይገኛል።
ኢትዮጵያም በታላቅ የሕዝብ ንቅናቄ እያሳረፈችው የምትገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የበረሃማነትን ስጋት ወደ ለምለም የልማት ዕድል ከመቀየር ባለፈ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፍ ታላቅና ዘላቂ ሀገራዊ ቅርስ ነው።
በመሐመድ ፊጣሞ