የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ ለረጅም ዘመናት የተተበተበውንና በብልሹ አሠራር ምክንያት የሪፎርም ዝለት ደርሶበት የነበረውን የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ትልቅ ታሪካዊ ሽግግር መደረጉን አበሰሩ፡፡
ከንቲባዋ ዛሬ በአቃቂ ቃሊቲ እና በለሚ ኩራ ክፍለ ከተሞች ሁለት አዲስ የ“አዲስ መሶብ” የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ማዕከላትን በይፋ መክፈታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በዚህም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሁሉም 11ዱም ክፍለ ከተሞች ማዕከላቱን ሙሉ በሙሉ እውን በማድረግ የገቡትን ቃል በተግባር ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል፡፡
ለውድ የከተማዋ ነዋሪዎች ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢ፣ ግልጽ እንዲሁም ከአድሎና ከጉቦ የጸዳ ፍትሐዊ አገልግሎት በሁሉም አካባቢ ማግኘት የሚያስችሉ ማዕከላትን በማግኘታቸው የተሰማቸውን ልባዊ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስተላልፈዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በእነዚህ ዘመናዊ ማዕከላት አማካኝነት ለሕብረተሰቡ 50 በመቶ ያህል የመንግሥት አገልግሎቶች እጅግ ቀልጣፋ በሆነ መልኩ እየተሰጡ እንደሚገኝ የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ የከተማ አስተዳደሩ ቀጣይ ስትራቴጂካዊ ትኩረት ቀሪዎቹን 50 በመቶ አገልግሎቶች ወደ እነዚህ ማዕከላት በማስገባት የአገልግሎት አሰጣጡን ሙሉ በሙሉ ማዘመንና ለነዋሪዎች የላቀ እርካታንና እፎይታን መፍጠር መሆኑን በቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
ይህ አዲስ አሠራር ሕዝባችን ጊዜውንና ገንዘቡን ለልማት እንዲያውል የሚያስችል ትልቅ እመርታ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ተቋማቱ በሀገር ውስጥ ሙያተኞች የተገነቡ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ሀገራዊ ሕልሞቿን በለውጥ ጉዞ ማሳካት እንደምትችል ዓይነተኛ ማረጋገጫዎች ናቸው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የዛሬዎቹን ማዕከላት ጨምሮ ፕሮጀክቶቹን በአጭር ጊዜና በጥራት በመገንባት፣ በማማከር እንዲሁም ተቋማቱ በቴክኖሎጂ እንዲሟሉ የበኩላቸውን የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ሁሉ በከተማዋ ነዋሪዎች፣ በከተማ አስተዳደሩና በራሳቸው ስም የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡