Search

በምክክር የምትጸና ኢትዮጵያ

ረቡዕ ሰኔ 17, 2018 121

የሰው ልጅ የሥልጣኔ ማማ፣ የእድገትና የመሻገር ሚስጥር መነጋገር፣ መደማመጥ እና የሀሳብ ልዕልናን ማክበር ነው። የኢትዮጵያ ያለፉት ዘመናት ፖለቲካዊ ታሪክ ግን ከዚህ የሥልጣኔ ጎዳና በእጅጉ ያፈነገጠ ነበር።

አንዱን ገሎ ስልጣን ላይ መውጣት፣ የተለየ ሀሳብን ማጥፋት፣ "የኔ ሀሳብ ካልሆነ" የሚል ጀብደኝነት፣ እና የስልጣን ምንጭን ከጠመንጃ አፈሙዝ ብቻ መፈለግ የፖለቲካችን መገለጫ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ሰው ወለድ ጭቆና እና ጠባብ የፖለቲካ እይታ፣ ሀገሪቱን በሁለት ጽንፍ የያዙ ነጠላ ትርክቶች እንድትታመስና የጋራ አገራዊ ትርክት እንዳይኖረን በማድረግ እጅግ ውድ ዋጋ አስከፍሎናል።

ዛሬ ግን የታሪክ ፀሐይ አዲስ ብርሃን ፈንጥቃ፣ የተስፋ በር ተከፍቷል። ላለፉት ዘመናት ውይይትን የሚጸየፍ እና የተለየ ሀሳብን የሚጠላ መንግስት በነበረበት ሀገር፣ ዛሬ የመመካከርን በሮች ወለል አድርጎ የከፈተ እና የሀገራችንን ቀሪ ዕጣ ፈንታ በጋራ እንወስን የሚል የለውጥ መንግስት እና ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ተፈጥሯል።

ከ2010 ዓ.ም ወዲህ የተወሰዱት የፖለቲካ እና የዴሞክራሲ ምህዳርን የማስፋት እርምጃዎች፣ ህዝቡ የዴሞክራሲን ጣዕም እንዲያውቅና ተስፋውን እንዲያለመልም አድርገዋል።

ስለሆነም፣ ይህ ትውልድ ከፊቱ ሁለት ግልጽና ወሳኝ ምርጫዎች ተደቅነውለታል። የመጀመሪያው የመፅናት መንገድ ነው፡ ወደ ሀሳብ ጠረጴዛ መምጣት፣ መወያየት፣ በመነጋገር ውስጥ የሀሳብ ልዩነቶችን ማጥበብ፣ የጋራ አቋም መያዝና ብሔራዊ መግባባት ፈጥሮ ሀገርን ማዳን ኢትዮጵያን ማጽናት ነው።

ይህ አካሄድ የተሰበረውን ሀገረ መንግሥት ለመጠገንና በህዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ብቸኛው አማራጭ ነው። ሁለተኛው ምርጫ ደግሞ የሃሳብ መድረክ አልባው የብቸኝነት የጥፋት መንገድ ነው። ውይይትን መግፋት፣ እንዳለፉት ጊዜያት እርስ በእርስ መጠፋፋት፣ እየተታኮሱ መኖር እና የደም ዘመን እንዲቀጥል ማድረግ ማለት ነው።

አሁን በተከፈተው የውይይት መድረክ ላይ አለመሳተፍ፣ ለመነጋገር ፈቃደኛ አለመሆን እና መመካከርን መጥላት ከዘመን ጋር አለመሻገር እና የኢትዮጵያ እድገትና ስልጣኔ ፀርነት ነው።

የሰላምን በር ዘግቶ የጥፋትን መንገድ መምረጥ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ታሪካዊ ስህተት ነው። ያልተመካከረ ለአሁኗ ኢትዮጵያ ውግዝ ነው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን የትላንት ገናና ታሪክ፣ ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር፣ በመከራም በደስታም አብሮ የመቆም ልምድ፣ እና እንደ ገዳ ሥርዓት ያሉ የዳበሩ ባህላዊ የዴሞክራሲ እሴቶች ያሉን ህዝቦች ነን።

እነዚህን ነባር እሴቶች ተጠቅመን፣ ሁሉንም ህዝቦች በእኩልነት የሚያስተናግድ አሳታፊና አካታች የሆነ የመግባባት ዴሞክራሲ ማነጽ ይጠበቅብናል።

በመሆኑም፣ ዛሬ ላይ ዴሞክራሲ፣ መወያየት እና ብሔራዊ ምክክር ለኢትዮጵያውያን የቅንጦት ወይም የውጭ ለጋሾችን የማስደሰቻ ጉዳይ ሳይሆን፣ ቃል በቃል የህልውናችን ጥያቄ ነው።

ጥቂቶች ብቻቸውን ሮጠው ሊያሻግሯት አይችሉም፤ ኢትዮጵያ የምትገነባውና የምትጸናው በሁሉም ልጆቿ የነቃ ትብብርና ተሳትፎ ብቻ ነው። እጣ ፈንታችን በእጃችን ነው፤ የተከፈተልንን የመመካከር ዕድል ተጠቅመን ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ ለመገንባት በአንድነት እንነሳ!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ