Search

በሀገር አቀፍ ደረጃ 2 ሺህ 300 የኃይል መሙያ ጣቢያዎች ሊገነቡ ነው

ዓርብ ሚያዝያ 09, 2018 211

ኢትዮጵያ ወደ አረንጓዴ ኢነርጂ እና ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የምታደርገውን ሽግግር ይበልጥ ለማፋጠን በሚቀጥሉት አስር ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ 2 ሺህ 300 ከፍተኛ አቅም ያላቸው ፈጣን የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት ማቀዷን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረኦ ሀሠን አስታወቁ።

ዕቅዱ ኢትዮጵያ ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጀመረችውን ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ወሳኝ እርምጃ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን እስካሁን ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ተወስኖ የነበረው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሠረተ ልማት አሁን ላይ ወደ ክልል ከተሞችና ዋና ዋና አውራ መንገዶች መስፋፋት መጀመሩም ተመላክቷል።

ሰሞኑን በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት በአዳማ ከተማ የተመረቀው የመጀመሪያው ፈጣን የኃይል መሙያ ጣቢያ ለዚህ እንደ ማሳያ የተጠቀሰ ሲሆን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ባለቤቶች ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ለጉዞ በሚወጡበት ወቅት የኃይል መሙያ ጣቢያዎች እጥረት ዋነኛ ፈተና ሆኖባቸው መቆየቱ ተገልጿል።

ተጠቃሚዎች ለሲጂቲ ኤን እንደገለጹት በመንገድ ላይ ኃይል በሚያልቅባቸው ወቅት ከግለሰቦች ኃይል ለመሙላት እስከ 2 ሺህ ብር የሚደርስ ያልተገባና የተጋነነ ክፍያ ይጠየቁ የነበረ ሲሆን ይህም ለተሽከርካሪ ባለቤቶች ኢኮኖሚያዊ ጫና ከመፍጠሩ ባለፈ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በልበ ሙሉነት ለመጠቀም እንቅፋት ሆኖ መቆየቱ ተጠቁሟል።

 አቶ በረኦ ሀሠን በአዳማ የተከፈተው ጣቢያ የግለሰቦችን ያልተገባ ብዝበዛና የደህንነት ስጋት የሚቀንስ መሆኑን ሲገልጹ ተጠቃሚዎችም በበኩላቸው መሰል ተቋማዊ የኃይል መሙያ ጣቢያዎች በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም በአስቸኳይ እንዲስፋፉ ያላቸውን ጉጉት ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ መንገዶች ላይ የሚንቀሳቀሱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 140 ሺህ በላይ መድረሱን የሚኒስቴሩ መረጃ የሚያመለክት ሲሆን ይህንን በፍጥነት እያደገ የመጣ ቁጥር የሚመጥን ዘመናዊ መሠረተ ልማት ለመዘርጋት መንግሥት 10 ዓመት መሪ ዕቅድ ነድፎ ወደ ተግባር ገብቷል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚገነቡት 2 ሺህ 300 ፈጣን የኃይል መሙያ ጣቢያዎች መካከል 1 ሺህ 176 በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነቡ ሲሆን የቀሩት ጣቢያዎች ደግሞ ዋና ዋና የሀገር አቋራጭ መንገዶችንና የክልል ከተሞችን በማስተሳሰር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ያለምንም ስጋት ከቦታ ቦታ እንዲንቀሳቀሱ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩ ታውቋል።

መንግሥት መሠረተ ልማቱን ይበልጥ ለማስፋፋት የግሉ ዘርፍ በስፋት ኢንቨስት እንዲያደርግ የሚያስችል መመሪያ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን በዚህም መሠረት ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ሌሎች የግል ባለሀብቶች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀርቧል።

አዲሱ ፖሊሲ ሆቴሎች፣ ሪል እስቴቶች፣ የነዳጅ ማደያዎችና የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች የራሳቸው የኤሌክትሪክ የኃይል መሙያ መገልገያዎች እንዲኖሯቸው የሚያስገድድ በመሆኑ የዘርፉ ተደራሽነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

አዳዲስ የሚገነቡት ጣቢያዎች ከመደበኛው ኃይል መሙላት ባለፈ ለተሽከርካሪዎቹ ቴክኒካዊ ምርመራ የማድረግ አቅም ያላቸው ሲሆን በአዳማ የተገነባው ዓይነት ዘመናዊ ማሽን ኃይል መሙላት ከመጀመሩ በፊት የባትሪውን ኬሚካላዊና ኤሌክትሪካዊ ሁኔታ የመተንተን እንዲሁም የሴሎችን አለመመጣጠን የማስተካከል አገልግሎት በነጻ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

ይህም የባትሪን ዕድሜ ለማራዘም እና ተሽከርካሪው በታማኝነት አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ከጥር 2024 ጀምሮ የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ የወሰደችው ቆራጥ ውሳኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈ ሲሆን አሁን እየተከናወኑ ያሉት ሰፊ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችም ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ ኢነርጂ ጉዞ ውጤታማ፣ አስተማማኝና ዘላቂ እንደሚያደርጉት ይታመናል።

ሃይማኖት ከበደ