Search

የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ፦ ከጠንካራ ፖሊሲ እስከ ስትራቴጂካዊ ውጤቶች

እሑድ ሚያዝያ 11, 2018 91

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በወንጪ-ደንዲ ተገኝተው የሀሮ ደንዲ ሎጅን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ ፖሊሲ፣ የማስፈጸሚያ ስትራቴጂ እና የተቋም አቅም በመገንባቱ አምስቱ የኢኮኖሚ ምሶሶዎች ከፍተኛ ስኬት እያመጡ መሆናቸውን አብራርተዋል። 

በንግግራቸውም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚውን የኢኮኖሚ ዕድገት እንድታስመዘግብ ያስቻሉ ዋና ዋና ጉዳዮችን እንደሚከተለው ዳስሰዋል።

የኢንዱስትሪ እና የግብርና ትራንስፎርሜሽን
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የሚገነባው መንግሥት ብቻ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን የግል ዘርፉ የራሱን ፓርኮችና በሺዎች የሚቆጠሩ ፋብሪካዎችን እንዲገነባ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል። 

ይህም ቀደም ሲል ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የወጪ ንግድን ለማሳደግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

በግብርናው ዘርፍም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተው በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ መደረጉን ጠቁመዋል። 

"በተለይ በቡና፣ በመስኖ እና በፍራፍሬ ልማት ላይ የግሉ ዘርፍ በስፋት መሰማራቱ ግብርናው ለሀገር ውስጥ ምግብ ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያም ትልቅ ምላሽ እንዲሰጥ አድርጎታል" ብለዋል።



የማዕድን እና የቴክኖሎጂ ዘርፍ እድገት
ማዕድን ቀደም ሲል ለኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦ ውስን እንደነበር የገለጹት ዶ/ር ዐቢይ፣ አሁን ግን በወርቅ፣ በማዳበሪያ፣ በጋዝ፣ በሴራሚክ እና በሲሚንቶ ምርቶች ላይ የግሉ ዘርፍ በስፋት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል። 

በተለይም በቅርብ ወራት ውስጥ ትልቁ የወርቅ ፋብሪካ እንደሚመረቅና የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታም ካለበት ፈጣን ጉዞ አንጻር ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተስፋቸውን ገልጸዋል።



በቴክኖሎጂው ዘርፍም የቴሌኮም ገበያውን ለግል ዘርፍ ክፍት በማድረግ የተፈጠረው ውድድር፣ የዳታ ተደራሽነትን ከማሳደጉ ባለፈ እንደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የ"5 ሚሊዮን ኮደሮች" ስልጠና ያሉ ተነሳሽነቶች ኢኮኖሚውን እያነቃቁት እንደሚገኙ አብራርተዋል።


የቱሪዝም ዘርፍ፦ "ዓይን ገልጦ የማሠራት ውጤት"
"በቱሪዝም ዘርፍ መቶ በመቶ ያቀድነውን አሳክተናል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት በ"ገበታ ለሀገር" እና "ገበታ ለትውልድ" መርሐ ግብሮች የመሠረተ ልማት አውታሮችን በማሟላቱ የግሉ ዘርፍ በስፋት እንዲገባ በር መክፈቱን ገልጸዋል። 

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ያላትን የእንግዶች መቀበያ የአልጋ አቅም ከ20 ሺህ ወደ 80 ሺህ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል። 

የደንዲ ሎጅ የሚገኝበት አካባቢ እንደ አባ መላ (ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ)፣ ገበየሁ ጉርሙ፣ ባልቻ አባ ነፍሶ እና ሌሎችም የኢትዮጵያን ነፃነት ያስጠበቁ ጀግኖች መፍለቂያ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህን የታሪክ መናሃሪያዎች ማልማት ታሪክን ለትውልድ ለማሸጋገር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።



የመሠረተ ልማት ትስስር እና የፈጣን መንገዶች ግንባታዎች
የመዳረሻ ቦታዎችን ከአዲስ አበባ ጋር ለማገናኘት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በተመለከተም፣ "አዲስ አበባን ማዕከል በማድረግ ወደ አምስቱም በሮች የ100 ኪሎ ሜትር መንትያ መንገዶችን (Highways) እየገነባን ነው" ብለዋል። 

ይህም ወደ አምቦ፣ ደብረ ብርሃን፣ ፊቼ፣ ወሊሶ እና አዳማ የሚደረጉ ጉዞዎችን በማቅለል የትራፊክ መጨናነቅን እንደሚቀንስና የቱሪስት ፍሰቱን እንደሚያሳልጥ ገልጸዋል።

"እንደ ንስር ወደ ከፍታ መብረር"
ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ኢትዮጵያ በ2026 በአፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት የምታስመዘግብ ሀገር መሆኗን መተንበያቸውን ጠቅሰዋል። 

ይህ ውጤት የመጣው በላብና በትጋት በመሥራት መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የንስርንና የቁራን ምሳሌ በመጥቀስ ኢትዮጵያ ለሚሰነዘሩባት ትናንሽ ትንኮሳዎች ምላሽ ሳትሰጥ ወደ ከፍታዋና ወደ ብልፅግና ህልሟ መብረሯን እንደምትቀጥል በአጽንኦት ተናግረዋል።

ሥራውን ላከናወኑ ዲዛይነሮች፣ ኮንትራክተሮች እና ባለሀብቶች ምስጋናቸውን በማቅረብ፣ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲያድግና የእያንዳንዱ ቤተሰብ ገቢ እንዲሻሻል በጋራ መስራት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።