Search

ሐሮ ደንዲ፡ በተፈጥሮ እጅ የተሳለችው የኢትዮጵያ ሰማያዊ ዕንቁ እና የጥንታዊ ታሪክ መገኛ

እሑድ ሚያዝያ 11, 2018 67

አስደናቂ የሆነውና ከወንጪ አስራ አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የደንዲ ኢኮ ሎጅ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።

የተፈጥሮ ሥጦታዋ ደንዲ

በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ደጋማ ቦታዎች ላይ የሚገኘውና በተፈጥሮ ውበቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት ሐሮ ደንዲ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ ውስጥ ይገኛል። ከአዲስ አበባ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ በግምት 127 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ይህ አስደናቂ ስፍራ፣ ከባሕር ጠለል በላይ 2 ሺህ 836 ሜትር ከፍታ ላይ በመገኘቱ ለየት ያለ ቀዝቃዛ አየር ንብረት እና ማራኪ እይታ አለው።

የሐሮ ደንዲ ዋነኛ መገለጫው "ቁጥር 8" ወይም የዱምቤል (Dumbbell) ቅርጽ ያለው መሆኑ ሲሆን፣ ይህ ቅርጽ የተፈጠረው ሁለት ክብ ቅርጽ ያላቸው የእሳተ ገሞራ አፎች በመካከላቸው ባለው ጠባብ መሬት አማካኝነት በመገናኘታቸው ነው። የሐይቁ ውኃ ሰማያዊ ቀለም ያለውና ጣፋጭ በመሆኑ ለተፈጥሮ አፍቃሪያን ልዩ እርካታን የሚሰጥ ሲሆን፣ ሐይቁ በደንዲ ካልዴራ ተከብቦ የሚገኝና በዝናብ ውኃ እንዲሁም በዙሪያው ባሉ ምንጮች የሚታደስ ድንቅ የተፈጥሮ ስጦታ ነው።

ከጂኦሎጂያዊ አመጣጥ አንጻር የደንዲ ካልዴራ የተፈጠረው 12 ሚሊዮን እስከ 1 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በነበረው የሌት ሚዮሲን (Late Miocene) እና የፕሊስቶሲን (Pleistocene) ዘመን በኃይለኛ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ ምክንያት ማግማ ከወጣ በኋላ ምድሩ ወደ ውስጥ በመደርመሱ ነው።

ይህ ስፍራ በተፈጥሮ ውበቱ ብቻ ሳይሆን በጥንታዊ የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ባለው ሚናም እጅግ ከፍተኛ ፋይዳ አለው። በኮሎኝ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ አካባቢው የጥንት ሰዎች መኖሪያ እንደነበር የሚያረጋግጡ 52 የአርኪኦሎጂ ስፍራዎች ተገኝተዋል።

የቅርስ ግኝቶቹ ዕድሜያቸው 200 ሺህ ዓመታት በላይ ወደኋላ (የአቺውሊያን ዘመን) የሚዘልቅ ሲሆን፣ ቀደም ሲል 2 ሺህ 500 ሜትር በላይ በሆኑ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ የጥንት ሰዎች አይኖሩም የሚለውን አስተሳሰብ የቀየሩ ናቸው። በአካባቢው የተገኙት የኦብሲዲያን (Obsidian) ድንጋይ መሣሪያዎች እና የአቺውሊያን (Acheulean) ሥልጣኔ ቅርሶች አካባቢው ለዘመናት የሰው ልጅ መሸሸጊያ ሆኖ ማገልገሉን ያረጋግጣሉ።

ከጥንታዊ ታሪክ ባለፈ፣ አካባቢው በቅርቡ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥም ትልቅ ቦታ ይዟል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) እንዳነሱት፣ ይህ ወንጪ፣ ደንዲ እና ወሊሶን የሚያካልለው አካባቢ የኢትዮጵያ ጀግኖች መናኸሪያ ነው። ኢትዮጵያን ጠብቀው ያቆዩት እንደ መጀመሪያው የመከላከያ ሚኒስትር ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) የአድዋው ጦር መሪ ፊታውራሪ ገበየሁ ጉርሙ፣ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎ (አባ ነፍሶ) ጀነራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ፣ ከበደ ቡዝነሽ እና ገረሱ ዱኪ የመሳሰሉ ጀግኖች መፍለቂያ መሆኑን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም ሐሮ  ደንዲ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ማዕከልም ጭምር ሲሆን፣ በአካባቢው የሚገኘውና 2 ሺህ 400 ሄክታር ስፋት ያለው የጭሊሞ ደን ለበርካታ ብርቅዬ እፅዋትና እንስሳት መኖሪያ ነው።

በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙት እንደ ሰማያዊ ክንፍ ያለው ዝይ (Blue-winged goose) ድኩላ አሞራ (Wattled ibis) እና ጥቁር ክንፍ ያለውፍቅር ወፍ (Black-winged lovebird) ያሉ አእዋፋት በአካባቢው በብዛት ይታያሉ። እንደ ዝግባ፣ ወይራ እና ኮሶ ያሉ የደጋማ ቦታዎች ዛፎች አካባቢውን አረንጓዴ አልብሰውታል። ይህም ደንዲን ለሳይንሳዊ ምርምርም ሆነ ለወፍ ምልከታ ተመራጭ ስፍራ ያደርገዋል።

ይህን የተፈጥሮና የታሪክ ጸጋ ለማልማት መንግሥት ከአምቦ እስከ ደንዲ፣ እንዲሁም ከወሊሶ እስከ ደንዲ ድረስ የመንገድ፣ የመብራትና የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን አሟልቷል። በዛሬው ዕለት ሚያዝያ 11 ቀን 2018 .. ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው በተሠሩ ልዩ ግንባታዎች ደምቆ የሚታየው እና ሁሉም መሰረተ ልማት የተሟላለት የደንዲ ኢኮ ሎጅ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ሌላው በረከት ሆኖ ተከስቷል። አካባቢው በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) እውቅናን ባገኘው "ወንጪ-ደንዲ" የቱሪዝም መንደር ፕሮጀክት ሥር መካተቱ ደግሞ፣ ስፍራውን የዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ አድርጎታል።

ለሚ ታደሰ