Search

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከኦስትሪያ አቻቸው ጋር ተወያዩ

ሰኞ ሚያዝያ 12, 2018 178

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከኦስትሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቤአተ ሜይንል-ሬይዚንገር ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ውይይት አድርገዋል። 

በውይይቱ ወቅት ሁለቱ ሚኒስትሮች በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል። 

በተለይም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በባህል እና በባለብዙ ወገን የትብብር መስኮች ገና ያልተነኩ ሰፊ ዕድሎች መኖራቸውን አስምረውበታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዎን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ስለ ኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ለሚኒስትሯ ገለጻ አድርገው፤ በተለይም በታዳሽ ኃይል፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በቱሪዝም እና በዲጂታል መሠረተ ልማት ዘርፎች ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን አንስተዋል። 

ሚኒስትር ቤአተ ሜይንል-ሬይዚንገር በበኩላቸው፤ አውስትሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማስፋት፣ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ማኅበረሰብ ትስስር ለማጠናከር፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ልዑካን ጉብኝቶችን ለማቀላጠፍ እንዲሁም በፈጠራ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በአቅም ግንባታ ዘርፎች ተቋማዊ አጋርነትን ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል። 

በተጨማሪም ዛሬ ቀደም ብሎ በተካሄደው የአውሮፓ ሕብረት-ኢትዮጵያ ቢዝነስ ፎረም ላይ የኦስትሪያ ኩባንያዎች የነበራቸው ተሳትፎ ውጤታማ እንደነበር መጠቆማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

#EBC #Ethiopia #Austria #Diplomacy #GedionTimothewos #EconomicReform