ትላንት የተመረቀው ውቡ የሀሮ ደንዲ ሎጅ ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ አዲስ ፋና ወጊ ከመሆኑም ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስተላለፉት መልዕክት የሀገራችንን ቀጣይ የጉዞ ፍኖተ-ካርታ አመላካች ነው።
"ኢትዮጵያ የምትሠራው በአባቶቻችን ደም ብቻ ሳይሆን በእኛም ላብ እንደሆነ ስለምናምን ነው" የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል፣ ኢትዮጵያ ካለባት የታሪክ እስረኝነት ወጥታ ወደ ተግባራዊና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ግንባታ መሸጋገሯን የሚያረጋግጥ ጥልቅ ፍልስፍናዊ መሠረት ነው።
ይህ እሳቤ አባቶቻችን በደማቸው ያስከበሩትን ነፃነትና ሉዓላዊነት፣ የዛሬው ትውልድ በላቡ ኢኮኖሚያዊ ልዕልናን በመገንባት ሊያፀናው እንደሚገባ የሚያስገነዝብ ወደ ልማት አርበኝነት የተደረገ የትኩረት ሽግግር ነው።
ይህንን የ“ላብ” ፍልስፍና በተግባር ከሚያረጋግጡ ደማቅ ማሳያዎች አንዱ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው ስር ነቀል ለውጥ ነው። ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየውንና ለድህነት ዳርጓት የነበረውን የኋላ ቀር እርሻ ዘይቤ በመቀየር፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀትና በቴክኖሎጂ በማገዝ በስንዴ ራስን የመቻል ህልሟን አሳክታለች።
ይህ ስኬት ህዝቡ በትጋት በመሥራት የምግብ ሉዓላዊነትን ለማሟላት የሚያደርገውን ያላሰለሰ ጥረት የሚያሳይ ነው። ከውጭ ጠባቂነት ወጥቶ ምርትን ወደ ውጭ መላክ መጀመር፣ ሀገርን በላብ የመገንባት እውነተኛ ማሳያ ነው።
በኢንዱስትሪው ዘርፍም “ኢትዮጵያ ታምርት” በሚለው ብሔራዊ ንቅናቄ የታገዘው ጥረት፣ የሀገር ውስጥ አምራችነትን በማጠናከር ረገድ ተጨባጭ ውጤቶችን እያሳየ ይገኛል። እንደ ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች በሁለት ዓመት ውስጥ ተገንብተው ለአገልግሎት ከመብቃታቸውም በላይ፣ በሲሚንቶ ምርት ላይ ተፈጥሮ የነበረውን እጥረት በዘላቂነት ፈትቷል።
ይህም መንግሥት ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በብቃት እና በፍጥነት የማጠናቀቅ ቁርጠኝነትን በተግባር ያረጋገጠበት ነው። በቀን 15 ሺህ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ይህ ፋብሪካ፣ የሀገራችንን የፍላጎትና የአቅርቦት ክፍተት በግማሽ በመሸፈን በገበያው ላይ የነበረውን ማነቆ ፈትቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት እና በቅርቡ የሚመረቀው ግዙፍ የወርቅ ፋብሪካ ኢትዮጵያ ሲባክን የነበረውን የወርቅ ሀብቷን በሥርዓት እንድትጠቀም የሚያስችል ነው።
በቱሪዝሙ ዘርፍ ከሸገር እስከ ደንዲ የደረሰው ስኬት ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምሥራች ፍሬ መቅመስ የጀመረችበት ነው። በዓመት ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ የመጡት በዚህ ረገድ በተሠራው ጠንካራ ሥራ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ“ላብ” ፍልስፍና አካላዊ ድካምን ብቻ ሳይሆን፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን የአዕምሮ ላብ እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምንም ያጠቃልላል። የ“5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች” ተነሳሽነት ወጣቶች በዲጂታሉ ዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የራሳቸውን የፈጠራ ውጤቶች እንዲያፈልቁ የሚያስችል ታላቅ ራዕይ ነው።
በርካታ ወጣቶች ሥልጠናውን ጀምረው በማጠናቀቅ የራሳቸውን የፈጠራ ሥራ እየጀመሩበት መሆናቸው ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አምራች ለመሆን የጀመረችውን ጉዞ የሚያፋጥን ነው።
ይህ በቴክኖሎጂ፣ በቱሪዝም ልማት፣ በማዕድንና በመሠረተ-ልማት የሚፈስሰው ላብ በድምሩ የኢትዮጵያን ብልፅግና በጠንካራ መሠረት ላይ እያቆመው ይገኛል።
በደንዲ የተላለፈው መልዕክት ለአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያውያን የቀረበ ሀገራዊ ጥሪ ነው። ያለፈው ታሪካዊ መስዋዕትነት ለነፃነታችን መሰረት እንደሆነ ሁሉ፣ የዛሬው ትጋታችንና ላባችን ደግሞ ለልጆቻችን የምናወርሳት የበለጸገች ሀገር ዋስትና ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ማጠቃለያ ላይ እንደጠቀሱት፣ እንደ ንስር አርቆ በማየትና ወደ ከፍታ በመብረር፣ የሚገጥሙ እንቅፋቶችን በሥራና በውጤት በማለፍ የኢትዮጵያን የላብ ውጤት ማሳየት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።
ይህ ትውልድ ከአባቶቹ የተረከባትን ሀገር በላቡና በዕውቀቱ አልምቶ ለቀጣዩ ትውልድ የማሸጋገር ታሪካዊ ግዴታውን እየተወጣ መሆኑን፣ በየዘርፉ የሚመዘገቡት ስኬቶች ህያው ምስክሮች ናቸው።
በለሚ ታደሰ