ሃይማኖት የነፍስ ማረፊያ፤ ባሕል የማንነት መስታወት፤ ስፖርት ደግሞ የወንድማማችነት አደባባይ ነው። እነዚህ ማህበራዊ ሀብቶቻችን የህብረብሔራዊቷ ኢትዮጵያ ህልውና መሰረቶች፣ የትውልድ ማሰሪያ ገመዶች ሆነው ዘመናትን ተሻግረዋል። ወደፊትም ይሻገራሉ።
ይሁንና፣ ዛሬ ላይ እነዚህ የንጹህ ልቦና መገለጫ የሆኑ ሀብቶች፣ ዘመን የተላለፋቸው የፖለቲካ ነጋዴዎች እና ቁማርተኞች የትኩረት ማዕከል ሆነው እናያለን። ይህ የሆነበት ምክንያት፣ እነዚህ ሀይሎች ፖለቲካን ከሀሳብ ልዕልና፣ ከራዕይና ከመርህ አውርደው ተራ የጥቅም መገበያያ የ"ፖለቲካ ማርኬት ፕሌስ" ወዳደረጉት የኪሳራ አዘቅት ውስጥ በመግባታቸው ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱን አንጻራዊ ሰላም ወደ አስተማማኝ ደረጃ ለማሸጋገር፣ ዘላቂ መረጋጋትን ለማስፈን እና ልማትን ለማፋጠን ሰፋፊ ስራዎችን ሰርቷል፤ ተጨባጭ ውጤቶችንም አስመዝግቧል።
የኢትዮጵያ አንጻራዊ ሰላም ከመቼውም ጊዜ በላይ መሻሻሉን ተከትሎ፣ በቅርቡ የተካሄደው ምርጫ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ያለ አንዳች ኮሽታና የጸጥታ እንከን ድምጹን መስጠቱ የዚህ ሰላም ትልቁ ማሳያ ነው። በየአካባቢው እንደ አደይ እያፈኩ ያሉ የልማት ስራዎችም ኢትዮጵያ የብልጽግና መንገድን መያዟን አፍ አውጥተው ይመሰክራሉ።
ይህ የህዝብ መረጋጋትና ሀገራዊ አቅም መጎልበት ግን፣ በሁከት ለሚነግዱ የፖለቲካ ደላሎች የእግር እሳት ሆኖባቸዋል።
እነዚህ የፖለቲካ ነጋዴዎች ከስሜትና ቀረርቶ ወጥቶ በአመክንዮ መሞገት ሲያቅታቸው፣ የህዝብን ስስ ብልት መፈለግ ጀመሩ። የሀይማኖት ተቋማትን እንደ ምሽግ፣ የትምህርት ማዕከላትን እንደ ጽንፈኝነት ማራቢያ፣ የእግር ኳስ ሜዳዎችን ደግሞ እንደ አጀንዳ ማራቢያ ላቦራቶሪ ለመጠቀም ሞከሩ።
ይህ ድርጊት በአጋጣሚ የተፈጠረ ሳይሆን፣ በጥልቅ የትርፍና ኪሳራ ስሌት የሚመራ የ"ፖለቲካ ማርኬት ፕሌስ" ጽንሰ-ሀሳብ መገለጫ ነው። በዚህ የፖለቲካ ገበያ ውስጥ፣ የተቀደሱ እሴቶች ይሸጣሉ፣ ግጭቶች ይቸረቸራሉ፣ ጥላቻ ደግሞ በከፍተኛ ዋጋ ይሸመታል። አላማውም በሕዝብ ማህበራዊ ሀብቶች ላይ በመቆመር የራሳቸውን የፖለቲካ ኪሳራ ማካካስ ነው።
ከዚህች ታላቅ ሀገር ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጦ ማሸነፍ እንደማይቻል ታሪክ ደጋግሞ አሳይቷል። የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያን የማዳከም፣ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንድትሰጥ የማድረግ እና በቀጠናው ያላትን የልዕልና ሚና የመቀማት ፍላጎታቸውን እውን ለማድረግ፣ አዳዲስ ስልቶችን ነድፈዋል። ፊት ለፊት መጥተው ማሸነፍ ስላቃታቸው፣ በጀርባ ዞረው በእነዚህ የውስጥ ባንዳዎችና የፖለቲካ ቁማርተኞች በኩል ማህበራዊ ስንጥቅ ለመፍጠር ይሞክራሉ።
እነዚህ የሀገር ውስጥ ተላላኪዎች፣ በሀይማኖት ካባ ተጀቡነው የታሪካዊ ጠላቶቻችንን ተልዕኮ የሚቀበሉና የሚያስፈጽሙ ናቸው። የሚያሳዝነው ደግሞ፣ ሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እና ቁስል እንዲፈጠር አድርገው፣ ተመልሰው በሌላ መስኮት "ተበደልን፣ አለቀልን" እያሉ አልቃሽ ሆነው በመምጣት እና ተበዳይ መስለው በመቅረብ የህዝብን ስሜት ለመስረቅ የሚሞክሩ መሆናቸው ነው።
መንግስት በእነዚህ የጥፋት ኃይሎች ሴራ እና ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ምክንያት በዜጎች ሕይወት፣ ንብረት እና ስነ-ልቦና ላይ በደረሰው ማንኛውም ጉዳት እጅግ በጥልቅ ያዝናል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከማንም በላይ ለዜጎቹ ደህንነትና ሰላም የሚቆረቆር እና የሚጠነቀቅ እንደመሆኑ፣ ይህንን የህዝብን ማህበራዊ እሴት የማፍረስ እና ዜጎችን የመጉዳት ተግባር በፍፁም ታግሶ አያልፍም። የህዝብን ደህንነት ለማረጋገጥ እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ሲል፣ በእነዚህ የፖለቲካ ቁማርተኞችና ተላላኪዎች ላይ የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል።
ህብረብሔራዊ አንድነቷ በተጠበቀ፣ የብዝሃነት ውበት በደመቀባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ማህበራዊ ተቋማትን መበከል ማለት የሀገርን የደም ስር እንደመቁረጥ ነው። እግር ኳስን የብሔር ግጭት ማራገቢያ፣ ሀይማኖትን የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ማስፈጸሚያ ማድረግ የሀገርን ሉዓላዊነትና የውስጥ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ተግባር ነው።
እነዚህ የጥፋት ሀይሎች የሚያልሙት ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳቸው ተጠራጥረው፣ ማህበራዊ እሴታቸው ተሟጥጦ፣ ሀገሪራቸውን ለውጭ ጠላት ተጋላጭ እንድትሆን ማድረግ ነው።
በእርግጥ ይህ የጥፋት ሴራ የሚሳካ አይደለም። ዛሬ ላይ ኢትዮጵያውያን የትላንቱን የታሪክ ስብራት እየጠገኑ፣ የነገዋን ብሩህ ሀገር ለመገንባት በሚያደርጉት ጉዞ ላይ እንዲህ አይነት ርካሽ የፖለቲካ ቁማሮችን በግልፅ ነቅተውበታል።
ህዝቡ ሀይማኖቱን ከፖለቲካ፣ ስፖርቱን ከሁከት እየለየ፣ አንድነቱን አጽንቶ የሴረኞችን ጥቃት በእንጭጩ እያመከነ ወደ ፊት እየተጓዘ ይገኛል። ማህበረሰቡ እነዚህ ፖለቲከኞች የሀሳብ ድርቅ የመታቸው እና ራዕይ የሌላቸው መሆናቸውን በሚገባ ተረድቷል።
በአጠቃላይ፣ ማህበራዊ ሀብቶቻችን የፖለቲካ ነጋዴዎች የገበያ ማዕከል የሆኑት፣ ፖለቲከኞቹ ሀገርን ከሚገነባ ሀሳብ ይልቅ አፍራሽ ትርፍን ስለመረጡ፣ እንዲሁም ፊት ለፊት ተጋፍጠው ኢትዮጵያን ማሸነፍ ስለማይችሉ ነው።
ይሁንና፣ በውሸት እንባ እያለቀሱ ሀገርን ለማፍረስ የሚሞክሩት እነዚህ ሀይሎች ሴራ፣ በማይበገረው የኢትዮጵያውያን አንድነት እና ጽናት ከንቱ መቅረቱ አይቀርም። ኢትዮጵያ የህብረብሔራዊነት ማማዋን፣ የልማት ጉዞዋን እና ሉዓላዊ ክብሯን አጽንታ፣ የፖለቲካ ቁማርተኞችን መረብ በጥሳ ጉዞዋን ወደ ብልጽግና ከፍታ አጠናክራ ትቀጥላለች።
በአዶኒያስ ወልደአረጋይ