ከስምንት አስርት ዓመታት በፊት ወደ ካይሮ ባደረገው የመጀመሪያ በረራ "አንድ" ብሎ ጉዞውን የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ ዛሬ ኢትዮጵያን ከዓለም ማገናኘት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን አቪዬሽን ወደ ላቀ ምዕራፍ ያሸጋገረ ግዙፍ ተቋም ሆኗል።
"አፍሪካውያንን እርስ በርስ ማገናኘት" (Bringing Africans Together) የሚለውን መሪ ቃል በተግባር ለመተርጎም፣ በስትራቴጂካዊ አጋርነት የአራት የአፍሪካ አገራትን አየር መንገዶች በማቋቋምና በማጠናከር ረገድ ቀዳሚውን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
አየር መንገዱ የሚከተለው ይህ የባለብዙ ማዕከል ስትራቴጂ፣ አፍሪካውያን የራሳቸው ጠንካራ የአየር ትራንስፖርት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ተኪ የሌለው አስተዋጽዖ እያበረከተ ነው። በዛምቢያ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የተመሰረቱት አየር መንገዶች የዚህ ስኬታማ ስትራቴጂ ትልልቅ ማሳያዎች ናቸው።
የአፍሪካ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካስመዘገባቸው ስኬቶች መካከል፣ የኤር ኮንጎ (Air Congo) ወደ ስራ መግባት በቅርቡ ጎልቶ የሚጠቀሰው ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ49 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያለውና በቴክኒክ፣ በስልጠና እንዲሁም በአመራር የሚደግፈው ኤር ኮንጎ፤ እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 01 ቀን 2026 ጀምሮ ከኪንሻሳ ወደ ብራሰልስ ቀጥታ በረራ እንደሚጀምር አስታውቋል።
ይህ በረራ ለዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ልዩ ትርጉም አለው። ለብዙ ዓመታት በደህንነት ስጋት ምክንያት የኮንጎ አየር መንገዶች ወደ አውሮፓ እንዳይበሩ ተጥሎባቸው የነበረውን እገዳ ለመሻገር ያስቻለው፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያቀረበው የ "Wet-lease" (አውሮፕላን ከነሙሉ ሰራተኞቹ የማከራየት) አገልግሎት ነው።
ይህም የደህንነት መስፈርቱን ለማሟላት ያስቻለ ሲሆን፣ አገልግሎቱም ዘመናዊ አውሮፕላን፣ ሙሉ የበረራ ሰራተኞች፣ የጥገና አገልግሎት እና የመድን (ኢንሹራንስ) ዋስትና አገልግሎቶችን ያካተተ ነው።
በረራው በዘመናዊው ቦይንግ 787-8 ድሪምላይነር አውሮፕላን በሳምንት አምስት ቀናት የሚከናወን ይሆናል። በዚህም ብራሰልስ አየር መንገድ ይዞት የነበረውን የገበያ የበላይነት በመስበር፣ ለአፍሪካውያን የተሻለ አማራጭና ተወዳዳሪ ዋጋ ይዞ ብቅ ብሏል።
ኤር ኮንጎ ከብራሰልስ በተጨማሪ ወደ ፓሪስ እና ዱባይ በረራዎችን ለመጀመር ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በአምስት አውሮፕላኖች (ሁለት ATR 72-600 እና ሶስት ቦይንግ 737-800) የሀገር ውስጥና ቀጣናዊ በረራዎቹን እያጠናከረ ይገኛል።
የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በቅርቡ በተከበረው የ80ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ ዛሬ የደረሰበት የላቀ ደረጃ የብዙዎች ላብና መስዋዕትነት ውጤት ነው። ለዚህ ስኬት ደግሞ በዋናነት የሚጠቀሱት መሠረታዊ ጉዳዮች ተቋሙ ያለው "ተቋማዊ ነፃነት"፣ ያልተቆጠበ የመንግስት ድጋፍ፣ አየር መንገዱ በንግድ መርህ ብቻ እንዲመራ መደረጉና የሚያገኘውን ትርፍ ለራሱ ማስፋፊያ እንዲጠቀምበት መፈቀዱ ናቸው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዛሬም እንደ ትላንቱ "የአፍሪካ አዲስ መንፈስ" (The New Spirit of Africa) ሆኖ ቀጥሏል።
የኤር ኮንጎ ወደ ብራሰልስ በረራ መጀመር የአንድ አየር መንገድ ስኬት ብቻ ሳይሆን፣ አፍሪካውያን በጋራ ከቆሙ ሰማዩም ቢሆን ጠባብ እንደማይሆንባቸው የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው።
አየር መንገዱ ለኢትዮጵያ የገጽታ ግንባታና ለኢኮኖሚ ጥንካሬ፣ ለአፍሪካ ደግሞ የትስስርና የኩራት ተምሳሌት ሆኖ መዝለቁን በኩራት እያረጋገጠ ይገኛል።
በላሉ ኢታላ