የዘመናት የታሪክ ማህደሯን ስንገልጥ ኢትዮጵያ የጀግኖች፣ በማዕበል የማይበገሩ አናብስት ምድር ሆና እናገኛታለን። የዛሬዋ ኢትዮጵያ የትላንት ታሪኳን ብቻ እየተደገፈች የምትኖር ሳትሆን፣ በተግባር የሚታይ፣ መሬት የረገጠ እና በዘመን የረቀቀ የማድረግ አቅም በተቋሞቿ በተለይም በመከላከያ ሠራዊቷ ላይ ገንብታለች።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በፅናት የጀመረችው ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ዕውን ሊሆን የሚችለው፣ ከመሰረቱ የማይነቃነቅ፣ ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚሰነዘርን ማንኛውንም ጥቃት ገና በእንጭጩ የሚያመክን አስተማማኝ የጸጥታ አቅም ሲገነባ ብቻ መሆኑን መንግስት በሚገባ ተረድቶ እየሰራ ይገኛል።
በዚህም መሰረት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከወትሮው በተለየ የመንግስትን ልዩ ትኩረት አግኝቶ፣ በከፍተኛ ሪፎርም እና ዘመናዊ አደረጃጀት ውስጥ አልፏል። ትላንት በአካላዊ ጥንካሬና በሞራል ብቻ ይዋጋ የነበረው ሰራዊታችን፣ ዛሬ የዘመኑን የሳይበር ደህንነት ቴክኖሎጂ የታጠቀ፣ በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች የተደራጀ እና ስነ-ልቦናዊ ልዕልናን የተላበሰ ሆኗል። በቅርቡ ከተለያዩ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች (እንደ ሁርሶ ማሰልጠኛ ያሉ) የተመረቁት የቁርጥ ቀን ልጆች የዚህ ሪፎርም ማሳያዎች ናቸው።
እነዚህ ወጣት መኮንኖች አካላዊ ብቃትን ብቻ ሳይሆን፣ ፈታኝ በሆኑ የጂኦ-ፖለቲካዊ ውጥረቶች ውስጥ ፈጣን እና ትክክለኛ ውሳኔ የመስጠት የአመራር ጥበብን የተላበሱ የዘመኑ አዋቂዎች ናቸው።
ይህ በልዩ ትኩረት የተገነባው የጸጥታ አቅም፣ በዋነኝነት "ዲተረንስ" (Deterrence) ወይም የማስቀረትና የመከላከል አቅምን ዓላማ ያደረገ ነው። አንድ ሀገር ጦርነትን የምታሸንፈው ጠላት መጥቶ ከተዋጋች በኋላ ብቻ ሳይሆን፣ ጠላት ጥቃት ለመሰንዘር ሲያስብ የሚያስከፍለውን ዋጋ ተረድቶ እንዳይመጣ በማድረግ ጭምር ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በቀጠናውና በጎረቤቶቹ ዘንድ የሚፈራ፣ ባለግርማ ሞገስ እና አንዳችም የውጭ ሀይል ሊደፍረው የማይችል ግዙፍ ክንድ ሆኗል። ይህ ዲተረንስ ሀገሪቱ የጀመረችውን የማክሮ ኢኮኖሚ፣ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር ያለ ምንም የደህንነት ስጋት በተረጋጋ ሁኔታ እንድታስቀጥል ብረት ለበስ ዋስትና ሰጥቷታል።
ከሁሉም በላይ ግን የዚህ ሪፎርም የተደረገበት ሰራዊት ትልቁ ትርጉም ከትውልድ ተልዕኮ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ መሆኑ ነው። ትላንት በ1960ዎቹ የነበረው የተሳሳተ ርዕዮተ-ዓለም የተጠናወተው ትውልድ፣ የራሱን መንግስት ለማፍረስ ሲል ከታሪካዊ የውጭ ጠላቶች ጋር በማበር የፈጠረው "የባንዳነት" ስህተት፣ ኢትዮጵያን ከባህር በር እንድትርቅ እና የሉዓላዊነት ስብራት እንዲገጥማት አድርጓል። ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሀገሪቱ በቀጠናው ትርጉም ያለው ሚና እንዳይኖራት፣ ተቆልፎባት በድህነት እንድትማቅቅ እና የራሷን የውሀ ሀብት (ዓባይን) እንዳትጠቀም ሸርበው ነበር።
ዛሬ ግን ያ የታሪክ ስብራት እየተጠገነ ነው። አሁን የተገነባው ሰራዊት የውስጥ ባንዳዎችንና የውጭ ጠላቶችን ሴራ ("ፅምዶ") በአንድነት አሽመድምዶ የጣለ፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የማይሰጥ የኢትዮጵያ አስተማማኝ አለኝታ ነው። ይህ ባለግርማ ሞገስ ሰራዊት፣ የትላንቱን ስህተት አርሞ የነገውን ብሩህ ተስፋ የሚያለመልም፣ በተለይም የዘመኑን ትውልድ የባህር በር ጥያቄ እና ሌሎች ቀጠናዊ የሉዓላዊነት እና የህልውና ስጋቶችን በብቃት፣ በእውቀት እና በማይበገር ጉልበት የመመለስ እና የማስጠበቅ ሙሉ አቅም አለው።
በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዛሬ ላይ የድንበር ጠባቂ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ የጀርባ አጥንት፣ የማድረግ አቅሟ ተምሳሌት እና የሉዓላዊነቷ የማይደፈር ማማ ነው። ጠላትን በርቀት የሚያስበረግገው ይህ የጀግኖች ስብስብ፣ ኢትዮጵያ በቀጠናው ያላትን ተፈጥሯዊ የልዕልና ቦታ እንድትይዝ እና የህዝቦቿን ጸጥታና ብልጽግና ለዘለዓለም አጽንታ እንድትቀጥል የሚያስችል የዘመናችን ህያው ጋሻ ነው።