የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፍ "ኢቲቱ" የተሰኘና ወተትን ለማርጋት የሚያስችል አዲስ የፕሮ ባዮቲክ እርሾ ይፋ አድርጓል።
ኢንስቲትዩቱ አዲሱን የምርምር ውጤት ይፋ ያደረገው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ እና የግብርና ድርጅት (FAO) እ.ኤ.አ በ2001 የመሠረተውን የዓለም የወተት ቀንን አስመልክቶ ዛሬ በተዘጋጀ የጋራ የውይይት መድረክ እና አውደ-ርዕይ ላይ ነው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ እንደገለጹት፤ "ኢቲቱ" የተሰኘው አዲሱ የፕሮ ባዮቲክ እርሾ በሀገራችን ያሉ የወተት ማቀነባበሪያ ድርጅቶች በውጭ ምንዛሪ ከውጭ አስገብተው የሚጠቀሙበትን እርሾ ሙሉ በሙሉ የሚተካ ነው።
ይህ ሀገር በቀል የምርምር ውጤት የወተት ማቀነባበሪያዎችን የውጪ ምንዛሪ ወጪ ከማዳን ባለፈ፣ ፓስቸራይዝድ የተደረገ ወተትን በአጭር ጊዜ ማለትም በአራት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ማርጋት እንደሚያስችል ተጠቁሟል።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ኢንስቲትዩቱ ምርምር ከሚያደርግባቸው የግብርና ውጤቶች ውስጥ ወተትና የወተት ተዋጽኦዎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ገልጸው፣ አዲሱ ምርት ለምግብ ዋስትና እና ለጤንነት ወሳኝ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን በጥራት የያዘ መሆኑን ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢንስቲትዩቱ የተሻሻሉ የሰብል እና የእንስሳት ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ለዘርፉ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የጠቀሱት ፕሮፌሰር ንጉሴ፤ በአሁኑ ወቅትም በወተት ምርታማነት ላይ ትኩረት ያደረጉና በባዮ ቴክኖሎጂ የታገዙ ልዩ ልዩ ምርምሮች በስፋት እየተከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።