Search

በየካ ክፍለ ከተማ የተገነባው ባለ 7 ወለል ዘመናዊ የ"አዲስ መሶብ" ዲጂታል የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ተመረቀ

ሰኞ ሰኔ 01, 2018 66

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሕዝብ የገባውን ቃል በተግባር መፈጸም ዋነኛ መለያው መሆኑን በመጥቀስ፣ በየካ ክፍለ ከተማ የተገነባውን 9ኛውን "አዲስ መሶብ" ዲጂታል የአንድ ማዕከል የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ማዕከል በዛሬው ዕለት በይፋ ሥራ ማስጀመሩን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ።

የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ፣ ፈጣን፣ ግልጽ እና ተደራሽ ለማድረግ በተያዘው እቅድ መሰረት፤ 2018 . በሁሉም ክፍለ ከተሞች "መሶብ ዲጂታል" የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስጀመር ለሕዝብ ቃል ተገብቶ በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከንቲባዋ አክለውም ይፋ በተደረገው እቅድና በተገባው ቃል መሰረት የዛሬውን ጨምሮ እስካሁን ድረስ 9 ግዙፍ ማዕከላትን ወደ ሙሉ ሥራ ማስገባት መቻሉን ገልጸዋል።

ይህ የዲጂታል አንድ ማዕከል አገልግሎት በዋናነት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ እንግልቶችንና በተለያዩ ቦታዎች የሚስተዋሉ የሙስና የመጠየቅ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ትልቅ ሚና ይኖረዋል እንደሚኖረው ነው ያመላከቱት።

ከዚህም ባሻገር በተቋማት ውስጥ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ የዜጎችን በክብር የመገልገል መብት ለማረጋገጥ እና ኅብረተሰቡ ለአገልግሎት ፍለጋ ጊዜውንና ገንዘቡን ሳያባክን ያለውን አቅም ለልማት እንዲያውለው ለማድረግ ታስቦ የተወጠነ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ግቦች በማሳካት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከንቲባ አዳነች አቤቤ አረጋግጠዋል።

በየካ ክፍለ ከተማ የተገነባውና ዛሬ በይፋ አገልግሎት መሥጠት የጀመረው ባለ 7 ወለል ዘመናዊ ሕንፃ በተያዘለት የጊዜ ገደብ በፍጥነት ተጠናቆ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲበቃ ከፍተኛ ጥረት ላደረጉና ሌሊትና ቀን ለደከሙ ባለድርሻ አካላት በሙሉ ከንቲባዋ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።