በኢትዮጵያ ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ በሁሉም ቦታ ተደራሽ ለማድረግ የፖሊሲና የቁጥጥር ሥርዓትን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።
ዛሬ በመላው ዓለም የሚከበረውን የዓለም የምግብ ደህንነት ቀን አስመልክቶ "ከምግብ ደህንነት ችግሮች ወደ መፍትሔዎች፤ በሁሉም ቦታ ደህንነቱ የተጠበቀ ምግብ" በሚል መሪ ሐሳብ ከተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ እንደተጠቆመው፤ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ስለ ችግሮች ብቻ ከማውራት ባለፈ ወደ ተግባራዊ መፍትሔዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።
በተለይም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የሚታዩት የመሠረተ ልማት እጥረት፣ የንጹሕ ውኃ አቅርቦት መጓደል እና በቂ ግንባታ የሌላቸው የገበያ ሥፍራዎች ለምግብ መበከል እና ለባክቴሪያዎች መራባት ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ መሆኑ ተነስቷል።
በመሆኑም መንግሥት እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ከእርሻ እስከ ማዕድ ያለውን የምግብ ሰንሰለት በጥብቅ መከታተል፣ ደረጃቸውን የጠበቁ መመሪያዎችንና ፖሊሲዎችን ማዘጋጀት እንዲሁም ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚጠበቅባቸው ተጠቁሟል።
የዓለም የምግብ ደህንነት ቀን ሲከበር ዕለቱን በማስታወስ ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋ በየቀኑ በሚያደርገው የምግብ ምርጫና ጥንቃቄ ለችግሩ መፍትሔ መሆን እንደሚችል መገንዘብ እንዳለበትም በመድረኩ ላይ መልዕክት ተላልፏል።
የዕለቱን መሪ ሐሳብ መነሻ በማድረግ ከችግሮች ወደ መፍትሔዎች ለመሻገር ምን ምን ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው የሚለው ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ ይህ የዓለም የምግብ ደህንነት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ8ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ7ኛ ጊዜ ተከብሮ ውሏል።
በዕድሉ ፈቀደ