ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የ2018 በጀት ዓመት የሦስተኛውን የ100 ቀን አፈጻጸም ሪፖርት ከፌደራል ተቋማት አመራሮች ጋር መገምገም ጀምረዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግምገማ መድረኩ መጀመሩን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በለውጡ አማካኝነት የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ በጽናት እያስቀጠለች መሆኑን ገልጸዋል።
መድረኩ የኢትዮጵያን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የመጻፍ ሂደት የሚፈተሽበት እና ትናንትን ከነገ ጋር የሚያስተሳስር ትልቅ መስታወት መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ናት፤ የሚገባትም ትልቅ ሥፍራ ነው፤ እኛ ደግሞ የዚህ ታሪክ ሠሪዎች የመሆን ዕድል በእጃችን ላይ ነው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ያልተጠናቀቀ የሀገረ መንግሥት ግንባታ እና የዴሞክራሲ እጦት ፈተና የነበሩ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ሀገራዊ ምክክር የተጀመረበት፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የጸደቀበት እና ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የጠናከረበት አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ መመቻቸቱን አብራርተዋል።
በተለይም ከለውጡ በፊት በፕሮጀክቶች ላይ ይስተዋል የነበረውን መዘግየት እና ብክነት በሥራ ዲሲፕሊንና በቅርብ ክትትል መስበር መቻሉን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት ማጠናቀቅ የመንግሥት መለያ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በኮሪደር ልማት፣ በገበታ ለሀገር እና በዲጂታል ኢትዮጵያ ዘርፎች የተካሄደው የመሠረተ ልማት አብዮት የኢትዮጵያን እና የከተሞቿን ገጽታ መቀየሩን በመልዕክታቸው አንስተዋል።
በተጨማሪም በስንዴ ልማትና በሌማት ትሩፋት አማካኝነት የተረጅነት ቀንበር ተሰብሮ ወደ ምግብ ሉዓላዊነት እየተጓዝን መሆኑን ጠቁመው፣ በዲፕሎማሲው መስክም ኢትዮጵያ ከእርዳታ ጠባቂነት ወደ ንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት በመሸጋገር ተደማጭነቷን ማሳደጓን ገልጸዋል።
በመሆኑም የዛሬው ትጋት ለነገው ትውልድ የሚተርፍ አሻራ በመሆኑ፣ ትልልቅ ፈተናዎችን በማሸነፍና ዕድሎችን በመጠቀም በሀገር ፍቅር መንፈስ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።