Search

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢንሼቲቭን ይፋ ሆነ

ማክሰኞ ነሐሴ 06, 2017 130

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለ25 ዓመታት የሚዘልቅ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢንሼቲቭን ዛሬ ይፋ አድርገዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢኒሼቲቭ ማብሰሪያ ኘሮግራም ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ  ኃላፊዎች በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

የህዝባችንን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፕሮጀክቶችን ከታሰበው ጊዜ ቀድሞ መጨረስን የመንግሥታችን ባህሪ ድርገናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ የኢትዮጵያን ሕልም እውን ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

ትልቅና ታላቅ ሀገር ለሆነችው ኢትዮጵያ እስካሁን የተሰራው ሥራ ብቻ በቂ አለመሆኑን በመጠቆምም ጉድለታችን ሰፊ ፣ ፍላጐታችን ትልቅና ህልማችን ሩቅ በመሆኑ በቀጣይ ብዙ ሥራ ይጠብቀናል ሲሉም ተናግረዋል።

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከመንግሥት በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት ኢንዱስትሪው ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ በመዳሰስ እ.አ.አ ከ2025 እስከ 2050 የሚዘልቅ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ኢንሼቲቭን በአጭር ጊዜ አዘጋጅቶ ለፍሬ ማብቃቱ የሚያስመሰግነው ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

ኢንሼቲቩ ተግዳሮቶችን የመንግሥት፣ የግል ወይም የሌላ የተለየ አካል ሳይል እንደ ሀገር የለየ፣ የኢንዱስትሪው ውጤታማነት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአህጉር ደረጃ ጉልህ ሚና እንዲጫወት የሚያስችል ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ተቋራጮችና አማካሪዎች ብቻ ሳይሆኑ አሠሪዎችም በየዓመቱ ተመዝነው ደረጃ የሚሰጥበት፣ ተጠያቂ የሚሆኑበት፣ ለሁሉም እንደየአፈፃፀሙ ዕውቅና የሚሰጥበት መሆኑ ኢንዱስትሪው በአጭር ጊዜ ውጤታማ፣ ለውጥ የሚታይበት፣ በአህጉር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችል አመላካች ነውም ብለዋል።

መንግሥት ከአሁኑ በበለጠ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን የሚያሳትፉ ሰፋፊ ሥራዎችን፣ ኘሮግራሞችን፣ ሜጋ ኘሮጀክቶችን ያቅዳል፤ በተከታታይም ይፋ ያደርጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የከተማና ልማት ሚኒስቴር እያደረገው ያለውን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ሊያጠናክር ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። 

በአሸናፊ እንዳለ

#ኢቢሲ #ኢቢሲዶትስትሪም #ኮንስትራክሽንኢንዱስትሪ #ትራንስፎርሜሽንኢኒሼቲቭ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ተያያዥ ዜናዎች: