Search

ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባሻገር የአንድን ሀገር ዓለም አቀፍ ተሰሚነት የሚያሳድገው የባሕር በር

ረቡዕ ጥቅምት 26, 2018 39

የባሕር በር ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው ሁሉ፣ አንድ ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖራትን የተሰሚነት ተፅዕኖ በአዎንታዊ መልኩ እንደሚያሳድገው በዘርፉ ጥናት ያደረጉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት በየትኛውም መመዘኛ ሕጋዊና ትክክለኛ ጥያቄ በመሆኑ ተገቢ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ሲሉ ነው ምሁራኑ የገለጹት።
የባሕር በር ቀጥተኛ የኢንቨስትመንት ዕድልን ከማስፋቱም ባሻገር የአንድ ሀገር ዳር ድንበር ተከብሮ እንዲኖር የሚኖረው ሚና ቀላል አይደለም ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ በተሸረበባት ሴራና በልዩ ልዩ በደሎች ከባሕር በር እንድትርቅ የተደረገበት ሁኔታ እጅግ የሚያስቆጭ ጉዳይ መሆኑን ምሁራን ይገልጻሉ።
ሆኖም አሁን በኃላፊነት ላይ ያለው መንግስት ለዘመናት ቁጭት የነበረውን የባህር በር ባለቤትነት አጀንዳን የህልውና ጉዳይ በማድረግ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘበው እያደረገ ያለበት ሁኔታ ይበል የሚያሰኝ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አበሻ ሺርኮ (ዶ/ር)፤ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄው የህልውና ጉዳይ ሆኖ ህጋዊነትን፣ ታሪክንና መልክዓ ምድርን መሰረት በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነትን በማለም የተነሳ በመሆኑ ተገቢ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው ሥነ-ዜጋ እና ስነ-ምግባር ትምህርት ክፍል የሰላምና ደህንነት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ወንድሙ አዴ፤ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር የወጣችበት ምክንያት ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት ያልተገኘለትና ምንም አይነት ማስረጃ የሌለው መሆኑም ለሁላችንም ጥያቄ ሆኗል ብለዋል።
የባሕር በር የማግኘቱ ጥያቄ በየትኛውም መመዘኛ ሕጋዊና በትክክለኛ ጊዜ የቀረበ ትክክለኛ ጥያቄ በመሆኑ ተገቢ የሆነ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።