ኢራቅ በዛሬው ዕለት ከቱርኪዬ ጋር አንድ የትብብር ስምምነት ተፈራርማለች።
የሁለቱን ሀገራት ባለስልጣናት ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፥ የቱርኪዬ ኩባንያዎች በኢራቅ እጅግ ውድ እና ተፈላጊ የሆኑትን የውኃ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ይገነባሉ።
በምላሹ ኢራቅ እነዚህን ፕሮጀክቶች ከነዳጅ ሽያጭ በምታገኘው ገቢ ፋይናንስ ታደርጋለች።

በስምምነቱ መሠረት በኢራቅ መንግሥት የሚቋቋመው የውኃ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ኮሚቴ ለቱርኪዬ ኩባንያዎች ጨረታ ያወጣል።
በጨረታው የሚያሸንፈው ኩባንያ ባግዳድ ለአንካራ ከምትሸጠው ነዳጅ የሚገኘውን ገቢ እየወሰደ በኢራቅ የውኃ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶቹን ይገነባል።
በመጀመሪያው ዙር የሚከናወኑት ሦስት የውኃ ማጠራቀሚያ ግድቦች እና ሦስት የመሬት ሙሌት ፕሮጀክቶች ናቸው።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የመጀመሪያው የውኃ ስምምነት ማዕቀፍ የተፈረመው እአአ በኤፕረል 2024 ፕሬዚዳንት ረጀብ ጣይብ ኤርዶኻን ባግዳድን በጎበኙበት ወቅት ነው።
ጉብኝቱ ውጥረት ነግሶበት ለዓመታት የዘለቀው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የተሸጋገረበት ነበር።
ከውኃ ሀብቷ 70 በመቶ የሚሆነውን ከጎረቤት ሀገራት፣ በተለይም ቱርኪዬን አቋርጠው ከሚፈሱት ጢግሮስ እና ኤፍራጥስ ወንዞች በምታገኘው ኢራቅ የተንሰራፋው የውኃ እጦት በሁለቱ ሀገራት መካከል ትልቅ ጉዳይ ነው።
በነስሩ ጀማል
#ebcdotstream #turkiye #iraq #deal #projects