Search

የባሕር በር እና የኢትዮጵያ ዕውነታ

ማክሰኞ ጥቅምት 25, 2018 40

ኢትዮጵያ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ የባሕር በሯን ያለአግባብ ተነጥቃ ቆይታለች። ይህም በንግድ ሒደት ላይ ያልተገቡ ተፅዕኖዎችን በመፍጠር ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ጥቅሞችን እንዳታገኝ ማድረጉን የዘርፉ ምሁራን ይገልፃሉ።
የዓለም አቀፉ የመርከብ ድርጅት ሚሪስክ የኢትዮጵያ ወኪልና የፍሬተርስ ኢንተርናሽናል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዳንኤል ዘሚካኤል ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር ማጣቷ በከፍተኛ መጠን ተጎጂ እንዳደረጋት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በታሪክ በቀይ ባሕር በኩል ወደብ እንደነበራት በግልጽ የተረጋገጠ መሆኑን የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ አሁን ላይ የተነሳው የይገባኛል ጥያቄም ፍትሐዊና ተገቢነት ያለው መሆኑን አስረድተዋል።
ሀገሪቷ በአሰብና በምፅዋ ወደቦች ላይ ከፍተኛ መሠረተ ልማቶችን የገነባች መሆኗ የባሕር በር እንደነበራት ሌላኛው አስረጂ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በነበሯት ወደቦች ላይ የነዳጅ ማጣሪያ መገንባቷን እንዲሁም ለወደብ ጥገና የሚያገለግል ስፍራና የኮንቴይነር ማከማቻ ግንባታዎችንም ጀምራ እንደነበር ጠቁመዋል።
ይሁንና ባልተገባ መንገድ የባሕር በር ያጣችው ኢትዮጵያ ጉዳዩ ኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩንም አብራርተዋል።
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊም የባሕር በር ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ እንዲመለስ እስከ መጨረሻው ሒደት ድረስ ጥረት ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል።
"የባሕር በር አልባ መሆን ሀገራችንን ምን ያህል እንደጎዳት አብዛኛው ሰው እንደሚረዳ የገለፁት አቶ ዳንኤል፤ ኢትዮጵያውያን ከዚህ ቀደም ለመብታቸውና ለሕልውናቸው ሲሉ ያደረጓቸውን ሰላማዊ ትግሎች የባሕር በርን ለማስመለስ በሚደረገው ጥረትም ሊደግሙት እንደሚገባ አመላክተዋል።
 
በላሉ ኢታላ