Search

ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ - አሰልጣኞች ስለ ምሽቱ ጨዋታ ምን አሉ?

ማክሰኞ ጥቅምት 25, 2018 39

የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን 6 ጊዜ ያነሳው ሊቨርፑል በውድድሩ 15 ጊዜ ሻምፒዮን ከሆነው ሪያል ማድሪድ ጋር ዛሬ ምሽት በአንፊልድ ከባድ ፍልሚያ ያደርጋል።
የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ዣቪ አሎንሶ ስለ ምሽቱ ጨዋታ በሰጠው አስተያየት፣ የዛሬው ጨዋታ በሻምፒዮናው ባለድል በመሆን ትልቅ ስኬት ባላቸው በሁለት ኃያል ክለቦች መካከል የሚደረግ ‘የአውሮፓ ኤል ክላሲኮ’ ነው ብሏል።
የምሽቱ ጨዋታ በደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ እግር ኳስ ወዳዶች ዘንድም ተጠባቂ መሆኑን ገልጿል።
"ከልብ የምወደውና በተጫዋችነት ዘመኔ ታሪክ በሠራሁበት ሊቨርፑል ቤት የሪያል ማድሪድ አሰልጣኝ ሆኜ መምጣቴ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው ያለው አሎንሶ፤ በደንብ ተጫውተን ውጤት ይዘን ለመመለስ ወደሜዳ እንገባለን" ሲል ተናግሯል።
የሊቨርፑል አሰልጣኝ አርን ስሎት በበኩላቸው፣ በአውሮፓ ለብዙ ዓመታት ውጤታማ ከሆነውን ጠንካራውን ሪያል ማድሪድ ጋር ነው የምንጫወተው፤ ዘንድሮም ከድንቅ ብቃት ጋር ውጤታማ ነው፤ ማድሪድ ትልቅ አሰልጣኝና ምርጥ ተጫዋቾች አሉት፤ ተጋጣሚያችንን እናከብራለን ብለዋል።
እኛም ግን ጠንካራ ቡድን ነን፤ ተጫዋቾችም ደጋፊዎችም ለክለቡ ውጤት ከልብ እንዲተጉ እጠይቃለሁ ሲሉ ተናግረዋል።
"አምና እኛ የገጠምነው የብዙ ተጫዋቾች ጉዳት የነበረበትን ማድሪድ ነበር አሁን ግን ብዙ ጉዳት የለባቸውም፤ ጨዋታው አቅማችንን በደንብ የምንለካበት ይሆናል" ብለዋል።
"ውጤቱም ከምሽቱ ጨዋታ በኋላ ይታያል" ሲሉ አርን ስሎት ተናግረዋል።
ሊቨርፑል እሁድ አስቶንቪላን ሲያሸንፍ ደጋፊዎች ያሳዩት ድጋፍ ለቡድኑ ውጤት ቁልፍ ነበር፤ ዛሬም እንዲደግሙት እጠይቃለሁ በማለት ተናግረዋል።
ሊቨርፑል ከሪያል ማድሪድ የሚያደርጉት ጨዋታ ዛሬ ምሽት 5 ሰዓት በአንፊልድ ይካሄዳል።
 
በላሉ ኢታላ