Search

የነገዋ ኢትዮጵያ፡ ከሀገራዊ ምክክሩ ማግሥት የሚፈነጥቀው አዲስ ተስፋ

ሰኞ ነሐሴ 18, 2018 42

የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ በአንድ ምዕራፍ የሚጠናቀቅ የፖለቲካ ሁነት ወይም በቃላት ብቻ የሚገለጽ ክስተት አይደለም።

ይህ ሂደት ባለፉት ዓመታት የተከማቹ የታሪክ ስብራቶችን፣ የትርክት ውዝግቦችን እና የመዋቅር ክፍተቶችን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ በመፍታት አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የከፈተ የለውጥ ጅማሮ ነው።

ይህ ታላቅ መድረክ ወደ ፍጻሜው ሲገሰግስ፣ የነገዋ ኢትዮጵያ ትልቁ ማሳያ "የእኔ ብቻ" ከሚል የጠበበ የፖለቲካ አመለካከት ወጥታ፣ የሁሉንም ሕዝቦች እና የማኅበረሰብ ክፍሎች ድምፅ ወደሚያዳምጥ አሳታፊ ሥርዓት የመሸጋገሯ ውጥን ነው።

ከዚህ ታሪካዊ ምክክር በኋላ ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በኃይል፣ በጥይት እና በግጭት ከመፍታት ይልቅ ውስብስብ ችግሮችን በሰለጠነ ውይይት የመፍታት አዲስ ባህልን እያጎለበተች ተቀጥላለች።

የፖለቲካ ሥልጣንም ሆነ ሕጋዊነት የሚመነጨው በጉልበት ሳይሆን በሕዝብ የነጻ ፈቃድ እና በተቋማት ጥንካሬ ላይ መሆኑን በተግባር ለማሳየት ጠንካራ መሰረት ተጥሏል።

ከምክክሩ የሚመነጩ ጠንካራ የውሳኔ ሀሳቦች ወደ ተግባር ሲቀየሩም፣ የሕግ የበላይነት፣ የሽግግር ፍትህ እና የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኝነት ይበልጥ ተጠናክረው ይቀጥላሉ።

በሌላ መልኩ ደግሞ የተገለሉ፣ ድምፃቸው ያልተሰማ ወይም ከሥርዓቱ ርቀው የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ በተለይም ወጣቶች እና ሴቶች፣ የፖለቲካው እና የኢኮኖሚው ዋና አቀንቃኝ የሚሆኑበት አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል።

ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ለኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ መሰረት ናቸው።

በመሆኑም ሀገራዊ ምክክሩ የሚያመጣው ማኅበራዊ መረጋጋት እና የሥነ-ልቦና ፈውስ፣ ኢትዮጵያ ቀድሞውንም ያላትን ግዙፍ የኢኮኖሚ አቅም ይበልጥ በማስፋት፣ በአፍሪካ ቀዳሚ የኢኮኖሚ ምሰሶነቷን እንድታጠናክር ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።

ይህንንም ተከትሎ እንደ 'ሌማት ትሩፋት' ያሉ የምግብ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጡ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች፣ ከሕዝቡ የነቃ ተሳትፎ ጋር ተደምረው ኢትዮጵያን ወደ ላቀ የብልጽግና ማማ ያሸጋግሯታል።

ከምክክሩ ማግሥት የምትገነባዋ ኢትዮጵያ ልዩነቶቿን እንደ ውበት እና ጥንካሬ የምትቆጥር፣ በጦርነት ፋንታ በሰላማዊ ውይይት የምታምን እና ለዜጎቿ እኩል ዕድልን የምታረጋግጥ ትሆናለች።

ከዚህም ባለፈ ለቀጣናው ብሎም ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የታላቅነት ምልክት እንዲሁም የምሥራቅ አፍሪካ የሰላም እና የትብብር ማዕከል ሆና ደምቃ የምትወጣ የጋራ ቤታችን ናት።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: