Search

የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ዲፕሎማሲ ከመከላከል ወደ ቀጣናዊ አጀንዳ ሰጪነት

ሰኞ ነሐሴ 18, 2018 51

በምሥራቅ አፍሪካ እና በቀይ ባሕር ቀጠና የተዘረጋው የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ከነበረበት ተከላካይነትና ምላሽ ሰጪነት ተላቆ፣ ቀጣናዊ ሁነቶችን ወደ መምራትና ሁለንተናዊ አጀንዳ ሰጪነት መሸጋገሩን የሚያሳዩ ማረጋገጫዎች እየጎሉ መጥተዋል።

ይህ ስትራቴጂካዊ ሽግግር እውን ሊሆን የቻለው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ፍላጎቷን የጠባብ ሙግት መነሻ አድርጋ ከማቅረብ ይልቅ፣ መላው ቀጠና ምላሽ ሊሰጠው የሚገባ የጋራ ጥያቄ እና የትስስር አመክንዮ አድርጋ በመቅረጿ ነው።

ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት የቀይ ባሕር ተፈጥሯዊ ወሰኗን በማስከበር የአዱሊስ፣ የምጽዋ እና የአሰብ ወደቦችን ስታስተዳድር እንዲሁም የዓለም አቀፍ ንግድ ዝውውርን ስታስጠብቅ የቆየች ታሪካዊ ሀገር ብትሆንም፣ በሒደት በታሪካዊ አጋጣሚዎች ከባሕር ተገልላ እንድትቆይ ተደርጓል።

ነገር ግን አሁን ላይ የያዘችው ግዙፍ የሕዝብ ቁጥር፣ ፈጣን የምጣኔ ሀብት ዕድገት እና የሎጀስቲክስ ፍላጎት ወደ ባሕር መስመሮች መድረስን የምኞት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ የመዋቅራዊ ሕልውና መሠረት አድርጎታል።

ሆኖም ኢትዮጵያ አጀንዳ የመቅረፅ ብቃቷን በግልጽ ያሳየችው የባሕር በር ጥያቄዋን ከጎረቤቶቿ ጋር እንደሚደረግ "የአንዱ ማግኘት የሌላው ማጣት" የሚሆን የውድድር ሜዳ አድርጋ አለማቅረቧ ላይ ነው።

ይልቁንም ጥያቄውን ከሰፊው የቀይ ባሕር ትስስር እና የጋራ ብልፅግና ራዕይ ጋር በማዋሃድ ቀጣናዊ ይዘት እንዲኖረው አድርጋዋለች።

በዚህም ምክንያት ውይይቱ ከጠባብ ሙግት ወጥቶ፣ ቀጣናው የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብታዊ ፍላጎት ከባሕር ዳርቻ ሀገራት ሉዓላዊነት እና ከሰፊው የቀይ ባሕር ደኅንነት ጋር የሚያስታርቅ አሠራር እንዴት ይገነባል ወደሚል ሰፊ የትብብር ማዕቀፍ ተሸጋግሯል።

ይህ ስትራቴጂካዊ ተፅዕኖ በተግባር ሊገለፅ የቻለው ኢትዮጵያ በሥራ ላይ ባዋለችው ገቢር-ነበብ የዲፕሎማሲ ስልት ነው።

የባሕር በር አጀንዳን በዲፕሎማሲው ጠረጴዛ ላይ በይፋ በማስቀመጥ የነቃ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ፍላጎቶቿን ለማስፈጸም የሚረዱ የፖሊሲ አማራጮችን ማስፋት፣ እና ዋና ዓላማውን ሳይስቱ ከወቅታዊው ሁኔታ ጋር አሠራርን ማላመድ መቻሏ የቀጣናው ፖለቲካ ዋና አጀንዳ ቀራጭ አድርጓታል።

ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነው ኢትዮጵያ የባሕር ኃይሏን ዳግም በጥንካሬ በማደራጀት የወሰደችው ስትራቴጂካዊ እርምጃ ነው።

የባሕር ኃይሉ ዝግጁነት በዓለም አቀፍ የንግድ መስመር ላይ የተደቀኑ ስጋቶችን፣ የባሕር ወንበዴነትን፣ ሕገ-ወጥ ዝውውርን እንዲሁም የሽብር እንቅስቃሴዎችን ከሥር ለማምከን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ወደ ባሕር የመድረስ ፍላጎት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ብቻ ሳይሆን፣ የቀይ ባሕርን የንግድ መስመር አስተማማኝ በማድረግ ለመላው ቀጣና ደኅንነት እና የጋራ አሸናፊነት የሚበጅ መሆኑን በተግባር ያረጋግጣል።

በሰለሞን ገዳ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: