የብሪክስ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የሴቶች ማብቃት ክፍል፣ በብሪክስ ፕላስ አባል ሀገራት የሴቶችን የቴክኖሎጂና የኢኮኖሚ ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር አዲስ አጠቃላይ የፖሊሲ ሰነድ ይፋ አድርጓል።
የዚህ አህጉራዊ የፖሊሲ ሰነድ ዋና አስፈላጊነት የተመሠረተው የሴቶች በስቴም (STEM) እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚኖራቸው ተሳትፎ የቁጥር ወይም የባዶ ውክልና ጉዳይ ብቻ አለመሆኑን በማረጋገጥ ላይ ነው።
ይልቁንም የሴቶች ንቁ ተሳትፎ የቀጣናውንና የዓለምን የኢኮኖሚ ውህደት እንዲሁም የፈጠራ አቅም የሚወስን ቁልፍ ሞተር መሆኑ ተስመሮበታል።
በመሆኑም ሴቶች በቴክኖሎጂና በፈጠራ ቅርፅ አወጣጥ ሂደት ውስጥ እኩል ካልተወከሉ በስተቀር የወደፊቱ የዓለም የፈጠራ አድማስ ሙሉ በሙሉ አሳታፊና ደጋፊ ሊሆን እንደማይችል ሰነዱ ያስረዳል።
ይሁን እንጂ ይህን እቅድ ወደ መሬት ለማውረድ በሴት ሥራ ፈጣሪዎች ላይ የተደቀኑ ሰባት መዋቅራዊ ፈተናዎችን በይፋ መለየት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ከእነዚህም መካከል ስር የሰደዱ ማህበራዊና ባህላዊ አመለካከቶች፣ የፋይናንስና የካፒታል አቅርቦት እጥረት፣ የባለቤትነትና የንብረት ጥበቃ ክፍተቶች እንዲሁም ያልተከፈለበት የሴቶች የቤት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ በይፋዊ የምርት መዝገብ ውስጥ አለመካተት በዋናነት ተጠቅሰዋል።
እነዚህ ተደራራቢ ችግሮች የሴቶችን እውነተኛ የፈጠራ አቅም ገድበው በመያዝ ለዘመናት በምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ የራሳቸውን አሉታዊ ጥላ ሲያሳርፉ ቆይተዋል።
እነዚህን ስር የሰደዱ መዋቅራዊ መሰናክሎች ለመሻገርና ከባዶ የጾታ እኩልነት መፈክሮች በመውጣት ሴቶች በትክክል የሚያስፈልጋቸውን ድጋፎች ለማሟላት ሰነዱ ግልጽ የሆኑ ተግባራዊ የመፍትሔ ስትራቴጂዎችን አመላክቷል።
ለዚህም ሲባል የሴቶችን የቴክኖሎጂና የሥራ ፈጠራ ጥረት የሚደግፍ የብሪክስ የሴቶች ፈጠራ ፈንድ ማቋቋም፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የዲጂታል ትምህርትን ማስፋፋት እንዲሁም ድንበር ተሻጋሪ የፈጠራ ማዕከላትን መክፈት በዋና ዋና የመፍትሔ አቅጣጫነት ተቀምጠዋል።
ይህ ይፋ የሆነው የፖሊሲ ሰነድ አባል ሀገራት በሴቶች የሚመሩ አዳዲስ ፈጠራዎችንና የሥራ እድሎችን በፋይናንስና በፖሊሲ ድጋፍ በማዘጋጀት፣ ዘላቂና አሳታፊ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችላቸውን አህጉራዊ ፍኖተ-ካርታ ያስቀመጠ መሆኑ ተገልጿል።
በሰለሞን ገዳ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: