Search

ኢጋድ በ7ኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ 26 የምርጫ ታዛቢዎችን ማሰማራቱን አስታወቀ

ቅዳሜ ግንቦት 22, 2018 37

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በሰባተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ በተለያዩ አካባቢዎች ከሴክሬታሪያቱና ከአባል ሀገራት የተውጣጡ 26 የምርጫ ታዛቢ ሙያተኞችን ማሰማራቱን አስታውቋል።

በኢጋድ የሰላምና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ እነዚህ የምርጫ ታዛቢዎች በአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢዎች መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ከአባል ሀገራት የምርጫ ቦርድ፣ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ከወጣቶችና ሴቶች አደረጃጀቶች ጋር በቀጥታ የሚሰሩ ሙያተኞች ናቸው።

በምርጫው ሂደት በተሰማሩት ታዛቢዎች ውስጥ የምርጫ ቦርድ ሙያተኞችና ኃላፊዎች ጭምር የሚገኙበት ሲሆን፣ በተመረጡ አካባቢዎች የታዛቢነት ስምሪት ተሰጥቷቸዋል።

ኢጋድ በዚህ ዓመት ብቻ የዑጋንዳንና የጂቡቲን አባል ሀገራት የምርጫ ሂደት መታዘቡን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያን 7 ጠቅላላ ምርጫ በሙያተኞች በማሰማራት እየታዘበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ታዛቢዎቹ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በሚያደርገው ቅድመ ዝግጅት የታዛቢነት መስፈርቶችን በማሟላት ምዝገባ አካሂደውና ቃለ መሃላ በመፈፀም ወደ ሥራ ገብተዋል።

ምርጫ ቦርድም ለምርጫ ታዛቢነት ላዘጋጃቸው አካላት የኢትዮጵያን የምርጫ ሕግና ሌሎች የአሰራር ደንቦችን የተመለከተ ስልጠና በመስጠት ፈቃድ መስጠቱን አብራርተዋል።