ኢትዮጵያ በታሪኳ አዲስ እና ደማቅ የዴሞክራሲ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። በመጪው ጠቅላላ ምርጫ ከ54 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ድምፃቸውን ለመስጠት መመዝገባቸው ከተራ አሃዛዊ ስኬት እጅግ የዘለለ ጥልቅ ትርጉም አለው።
ይህ አሃዝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሀገሩ ያለውን ፅኑ አቋም የሚያሳይ ሕያው ምስክር ነው።
ታዲያ የዚህ ግዙፍ ሕዝባዊ ተሳትፎ ትርጉም ከሉዓላዊነት እና ከሀገረ መንግሥት ግንባታ አንፃር ሲመዘን ምንን ያመለክታል?
1. ሉዓላዊነትን በተግባር ማረጋገጥ
በተለምዶ ሉዓላዊነት ሲባል ድንበርን ከውጭ ጠላት መከላከል ብቻ ተደርጎ ይወሰዳል። ነገር ግን የዘመናዊ ሉዓላዊነት መሠረት የሕዝብ ሕጋዊ ይሁንታ ነው።
54 ሚሊዮን ዜጎች የሀገራቸውን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ወደ ምርጫ ኮሮጆ ሲያመሩ ሉዓላዊ የውሳኔ ሰጪነት ሥልጣናቸውን በተግባር እያረጋገጡ ነው።
ይህ ግዙፍ ተሳትፎ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚያስተላልፈው አንድ ጥብቅ መልእክት አለ፡፡
ይኸውም የኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅጣጫ የሚወሰነው በራሷ ልጆች እንጂ በውጭ ኃይሎች ጫና ወይም ጣልቃ ገብነት አለመሆኑን ነው።
ይህ የሕዝብ ድምፅ የውጭ ጫናዎችን የሚመክት የሉዓላዊነት የማይበገር ጋሻ ነው።
2. ለሀገረ መንግሥት ግንባታ (State-Building) የጀርባ አጥንት መሆን
ኢትዮጵያ ለዘመናት በተወሳሰቡ የፖለቲካ ሽግግሮች፣ የታሪክ ስብራቶች እና የውስጥ ግጭቶች ውስጥ አልፋለች።
ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ለመገንባት የተበታተኑ ማንነቶችን እና አግላይ የፖለቲካ ትርክቶችን ወደ አንድ ማዕከላዊ የሕዝብ ውክልና ማምጣት የግድ ይላል።
የምርጫ ሳጥን ደግሞ ትልቁ የማስተሳሰሪያ ድልድይ ነው። ዜጎች በዚህን ያህል ታላቅ ቁጥር ሲሳተፉ የጥይት ድምፅን በካርድ፣ ሽኩቻን በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እየቀየሩት ነው።
ይህ የጋራ ርብርብ የተሰበረውን የማኅበራዊ ውል የሚጠግን፣ ማዕከል እና ዳርቻን የሚያስተሳስር፣ እንዲሁም የዴሞክራሲ ተቋማትን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆም ታላቅ ተግባር ነው።
3. የውክልናው ታሪካዊ ኃላፊነት እና የሕዝብ አደራ
ከ54 ሚሊዮን መራጮች የሚገኝ ውክልና እጅግ ከባድ የሆነ የኃላፊነት ሚዛን አለው። ይህ ድምፅ ለአሸናፊዎች የሚሰጥ ነፃ ፈቃድ ሳይሆን ጥብቅ የትውልድ አደራ ነው።
በእንደዚህ ዓይነት ግዙፍ ሕዝባዊ መሠረት ላይ የሚዋቀር መንግሥት የሕግ የበላይነትን የማስከበር፣ የኑሮ ውድነትን የሚቀርፍ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን የማረጋገጥ እና ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ መግባባትን የመፍጠር ብቃት ያጎናፅፈዋል፡፡
በአጠቃላይ ከ54 ሚሊዮን በላይ መራጮች መኖራቸው ተወካዮችን ከመምረጥ የዘለለ ትልቅ ሀገራዊ ፋይዳ አለው።
ይህ አሃዝ የኢትዮጵያ ሕልውና የማይናወጥ መሆኑን የሚያሳይ ማኅተም ነው። ሀገራችንን የመፈወስ፣ መልሶ የመገንባት እና ወደ ላቀ ከፍታ የማሸጋገር ኃይል ሙሉ በሙሉ በዜጎቿ እጅ መሆኑን የሚያበስር የንቃት ጊዜ ነው።
እነዚህ 54 ሚሊዮን ድምፆች መንግሥትን ብቻ ሳይሆን፣ ሉዓላዊ፣ ጠንካራ እና የተዋሐደች የነገዋን ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት አጥብቀው እየገነቡ ነው፡፡
በአዶኒያ ወልደአረጋይ