Search

በዲጂታልና በአካል የምርጫ ካርድ የወሰዱ አካል ጉዳተኞች ዝግጁነት

ቅዳሜ ግንቦት 22, 2018 8

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ አካል ጉዳተኞች በአካልና በዲጂታል አማራጮች በመመዝገብ የመራጭነት ካርዳቸውን በመውሰድ ድምፅ ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪና የመንግሥት ሠራተኛው አቶ ተግነው ተሾመ ለኢቲቪ በሰጠው አስተያየት፤ ምርጫ የተረጋጋ የፖለቲካ አውድ ለመፍጠር፣ በሕዝብ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመመሥረትና ዘላቂነት ያለው ሰላምን በማፅናት በኩል ያለው ሚና አይተኬ መሆኑን ተናግሯል።

ባለፉት ሁለት ምርጫዎች ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታውን መወጣቱን የገለጸው አቶ ተግነው፤ ቀደም ሲል የነበረው የአካል ጉዳተኝነት ችግር እንደልብ ተሯሩጦ ለመምረጥ ተግዳሮት ሆኖበት እንደነበር አስታውሷል።

አሁን ላይ ግን እሱን ጨምሮ ሌሎች አካል ጉዳተኞች በተፈጠረው ምቹ አሠራር በመታገዝ በንቃት በመመዝገብ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውንና የምርጫዋን ቀን በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን አብራርቷል።

በዕለቱም በጥዋቱ በምርጫ ጣቢያ በመገኘት የአካል ጉዳተኞችን መሠረታዊ ጥያቄዎች የሚመልስ እንዲሁም ለሀገራችን ሁለንተናዊ ጥቅም የሚሰራ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀቱን አስታውቋል።

አንድ ድምፅ ከፍተኛ ዋጋ ያላት በመሆኑ መላው ማህበረሰብ በእጁ ያለውን ካርድ በመጠቀም ግንቦት 24 ቀን 2018 . ይበጀኛል ይሆነኛል የሚለውን ፓርቲ እንዲመርጥም ጥሪ አቅርቧል።

በተስፋሁን ደስታ